እድገት የመብጥ ጥሰት መሸፈኛ ሊሆን አይገባም ተባለ

በሰብአዊ መብት፤ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ኪሳ የሚመጣ የምጣኔ ሀብትና የቁጥር እድገት ለህዝብ ጎጂ ነው፤ ሲሉ የሂውመን ራይትስ ወች የአፍሪካ ክፍል ሀላፊ አቶ ዳንኤል በቀለ ተናገሩ።
ምርጫ 97ን ተከትሎ ከፖለቲካ መሪዎችና ከፖለቲከኞች ጋር ለሁለት አመታት ታስረው የነበሩት አቶ ዳንኤል በቀለ በኒው ዮርክ ታይምስ ላይ በጻፉት ጽሁፍ፤ ለጋሽ አገሮች ገንዘባቸውን መሪዎች የፖለቲካ ስልጣን እንዲያጋብሱበት ካደረጉ፤ መርዳት የፈለጉትን ህዝብ ይጎዳል ሲሉ ተናግረዋል።
የሩዋንዳ፤ የኢትዮጵያን፤ የካምቦዲያ፤ የቬትናምና የሌሎች የሶቪየት ህብረት አካል የነበሩ አገራትን ተሞክሮ እንደምሳሌ የጠቀሱት  አቶ ዳንኤል፤ እነዚህ አገሮች የኢኮኖሚ እድገት ቢያሳዩም፤ የሰብአዊ መብት አያያዛቸው ግን አሽቆልቁሏል ብለዋል።
በነዚህ አገሮች፤ ጋዜጠኞች ይታሰራሉ፤ ይሰደዳሉ፤ ሰላማዊ ተቃውሞዎችም ይታፈናሉ፤ የሽብርተኝነት ክሶች ለማስፈራሪያነት ይውላሉ፤ ጋዜጦች ያታገዳሉ፤ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችም እንዳይነቀሳቀሱ ይሸበባሉ ሲሉ ጽፈዋል።
ለጋሾች መከተል ያለባቸው አንደኛ መብትን መሰረት ያደረገ እድገትና እርዳታ መሆን ሲገባው፤ ሁለተኛም መብትን መሰረት ያደረገ እድገት ለመረጃ ፍሰትና ለህግ የበላይነትና ለተጠያቂነትና ለህዝብ ተሳትፎ አስፈላጊ ሆኖ ሳለ፤ በተቃራኒው የአውሮፓና የአሜሪካ መንግስታት በሰብአዊ መብት ኪሳራ ለጸጥታና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ቅድሚያ መስጠታቸው አርቆ ያለማሰብ ችግር ነው ሲሉ ተችተዋል።
ይህ አይነቱ አርቆ አሳቢነት የጎደለው አካሄድ፤ ግጭትንና አለመረጋጋትን ስለሚያመጣ፤ ምእራባዊያን መንግስታትና አለማቀፍ ለጋሾች በኢትዮጵያና በሩዋንዳ ሰብአዊ መብትን የጠበቀ የኢኮኖሚ እድገት እንዲመጣ መስራት አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።