(ኢሳት ዲሲ–ጥር 13/2011)የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአልሻባብ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ማድረሱን መንግስት አስታወቀ።
አልሻባብ 50 የኢትዮጵያን መንግስት ወታደሮች ገደልኩ ባለ ማግስት የወጣው የኢትዮጵያ መንግስት መግለጫ 66 የአልሻባብ ወታደሮች መገደላቸውን ያትታል።
ከሶማሊያ መንግስት ጦር ጋር በጥምረት ተካሄደ በተባለው በዚሁ ጥቃት ከኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች በኩል የደረሰው ጉዳት አልተገለጸም።
አልሸባብ ገደልኳቸው ስላላቸው የኢትዮጵያ ወታደሮችንም በተመለከተ ምላሽ አልሰጠም።
አሜሪካንም በአልሸባብ ላይ ጥቃት መፈጸሟን አስታውቃለች።
ባለፈው ዓርብ አንድ የሶማሊያ የፕሬስ ውጤት የአልሻባብ ኮማንደርን ጠቅሶ ከፍተኛ ኪሳራ በኢትዮጵያ ሰራዊት ላይ ማድረሱን ዘግቦ ነበር።
በዚሁ የፕሬስ ውጤት ላይ እንደተመለከተው አልሻባብ ወደ ባይደዋ እያመራ የነበረና አራት አጀብ ወታደራዊ ኦራል ተሽከርካሪዎች የሚገኙበትን የኢትዮጵያ ሰራዊት በደፈጣ አጥቅቶ 50 ወታደሮች ተገድለዋል። ሁለቱ ተሽከርካሪዎች ወድመዋል።
ዘገባውን በሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ላይ ማረጋገጥ ባለመቻሉ የመረጃውን እውነተነኝነት ለማወቅ አስቸጋሪ አድርጎት ነበር።
በወቅቱ የሰላም አሰከባሪው ዘመቻ አሚሶምም ሆነ የኢትዮጵያ ሰራዊት በአልሻባብ ጉዳት አደረስኩ በተሰኘው መረጃ ላይ ማስተባበያም ማረጋገጫም ሳይሰጡ ቀርተዋል።
በትላንትናው ዕለት ግን የኢትዮጵያ መንግስት አልሸባብ ላይ ጠንካራ ምት ሰነዘርኩ የሚል መግለጫ ሰቷል።
ከሶማሊያ መንግስት ጦር ጋር በጥምረት በወሰድኩት ርምጃ በአልሸባብ ሃይል ላይ ከፍተኛ ኪሳራ አድርሻለሁ የሚለው መግለጫው በቪዲዮ ምስል ተደግፎ የወጣ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግስት በአልሸባብ ላይ በተወሰደው ርምጃ 66 ታጣቂዎቹ መገደላቸውንም ገልጿል።
ዓርብ ዕለት አልሸባብ አደረስኩ ስላለው ጥቃት የትላንቱ የኢትዮጵያ መንግስት የሰጠው ምላሽ የአልሸባብ የጥቃት ሙከራን በማክሸፍ አከርካሪውን ሰብረን መልሰነዋል የሚል ነው።
በሁለቱ ወገኖች በኩል የሚቀርበውን መረጃ በሶስተኛ ወገን ማረጋገጫ አልተሰጠውም።
በተያያዘ ዜናም አሜሪካ አልሸባብ ላይ የአየር ላይ ጥቃት መሰንዘሯ ተገልጿል።