የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ ተቃውሞ ማስነሳቱ ተሰማ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 13/2011)ባለፈው ሳምንት የጸደቀው የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ የጋምቤላ ነዋሪዎችን ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው በሚል ተቃውሞ ተነሳ።

የአኝዋክ ተወላጆች የመኖር ህልውናችንን አደጋ ላይ የሚጥል አዋጅ ነው ሲሉ በምሬት በመቃወም ላይ ናቸው።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው  የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ በአኝዋኮች ህልውና ላይ የተነጣጠረ አደጋ ነው ሲሉ ዶክተር አጆት ሚሩ የሰላምና የሰብዓዊ መብት ተመራማሪ ለኢሳት ገልጸዋል።

በአዋጁ  መሰረት ከጋምቤላ ነዋሪዎች ቁጥር የሚበልጡት የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ከሃገሩ ዜጋ እኩል የሚጋሯቸው ብዙ መብቶችን ያለገደብ እንዲጎናጸፉ መደረጉ አደጋውን የከፋ ያደርገዋል ብለዋል ዶክተር አጆት።

በ2016 የኢትዮጵያ መንግስት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ስደተኞችን በተመለከተ በዓለም መድረክ ፊት ቃል መግባቱ ነው ባለፈው ሳምንት ለጸደቀው የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ መነሻ ምክንያት የሆነው።

በዚሁ ጉባዔ ላይ ወደ አንድ ሚሊየን የሚጠጋ ስደተኞችን እያስተናገደች ያለችው ኢትዮጵያ ለስደተኞች ጥበቃና ከለላ እንዲሁም መብቶችን የሚፈቅድ አዋጅ እንድታወጣ አስገዳጅ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ነው በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች የሚገልጹት።

ዶክተር ኦጆት ሚር በዘርፉ ዓለም አቀፍ ጥናት አድርገዋል።

ኢትዮጵያ ለሰብዓዊ መብቶች ያላትን አወንታዊ አመለካከት ማሳየቷ የሚያስመሰግናት መሆኑን በመግለጽ ይጀምራሉ።

ይሁንና ባለፈው ሳምንት የጸደቀው የስደተኞች አዋጅ ግን የሌላውን መብት ለመጠበቅ የሀገሩን ሰው በስጋት ውስጥ መጣል መሆኑ ነው አስቸጋሪው ነገር ይላሉ።

ዶክተር ኦጆት አዋጁ ላይ ላዩን መጥፎ ነገር እንደሌለው ይገልጹና ከአቅሙ በላይ ስደተኞችን ያስጠጋው የጋምቤላ ክልል ጉዳይ ከግምት አለመግባቱ የአዋጁን ክፍተት ያሳያል ይላሉ።

የጋምቤላ ህዝብ ቁጥር ከ300ሺህ ብዙም ፈቅ አይልም። በአሁኑ ሰዓት ከደቡብ ሱዳን ተፈናቅለው በጋምቤላ የሚገኙት ስደተኞች ቁጥር ግን 407ሺህ ደርሷል።

ከሀገሩ ዜጋ በአንድ መቶ ሺህ የሚልቅ ስደተኛ በሚኖርባት ጋምቤላ አዋጁ በተለይ ለአኝዋክ ተወላጆች የህልውና አደጋ የሚደቅን እንደሆነ ነው ዶክተር ኦጆት የሚገልጹት።

በፓርላማ አንድም የጋምቤላ ተወካይ ባልመከረበት፣ ስለጉዳዩ እውቀትና መረጃ በሌላቸው የምክር ቤቱ አባላት ይሁንታ መጽደቁ ታሪካዊ ስህተት እንደሆነ አጽኖት በመስጠት ይናገራሉ።

ስደተኞቹ እስከዜግነት የማግኘት መብት ተፈቅዶላቸው ከትምህርት አንስቶ ስራ የመቀጠርና ሀብትና ንብረት የማፍራት እኩል መብት ከተሰጣቸው የክልሉ ነዋሪ በቀጣይ በስደተኞች ተውጦ በሀገሩ ባይተዋር የሚሆንበት አደጋ ተደቅኗል ይላሉ።

ቁራሽ መሬት ላይ ከሀገሩ ዜጋ የበለጠ ስደተኛ እንዲሰፍር መደረጉ ወደፊት ከፍተኛ ቀውስ እንደሚፈጥር ዶክተር ኦጆት ስጋታቸውን ይገጻሉ።

ከኢኮኖሚና ከተለያዩ መብቶች ባሻገር ስደተኞቹ የታጠቁ መሆናቸውን የሚጠቅሱት ዶክተር ኦጆት ይህ ሌላው የአዋጁ ክፍተት እንደሆነ ያስቀምጣሉ።

ስደተኛ ወደ ሁለተኛ ሃገር ሲሄድ መሳሪያ ታጥቆ መሆን እንደሌለበት እየታወቀ ጋምቤላ የሚገኙት የደቡብ ሱዳን ስደተኞች እስከነትጥቃቸው መግባታቸው ለሀገሬው የአኝዋክ ተወላጆች ከፍተኛ ስጋት የሚፈጥር ነው ብለዋል።

መንግስት ይህን እያወቀ የአኝዋኮችን ድምጽ እንዲዳፈንና ለስጋት እንዲጋለጡ ማድረጉ የሚወገዝ ርምጃ ነው ብለውታል።

ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የጋምቤላውን ስደተኛ የሚያስተናግዱና ሸክሙን ከጋምቤላ ላይ የሚቀንሱበት አሰራር ካልተዘረጋ በስተቀር በዚህ መልኩ የስደተኞችን አዋጅ ማጽደቁ ችግሩን ከማባባስ ባለፈ አዳዲስ ቀውሶችን እንደሚፈጥር ዶክተር ኦጁት ያስጠነቅቃሉ።

መንግስት አዋጁን ወደ ተግባር ከመለወጡ በፊት ማስተካከያ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

የአኝዋክ ማህበረሰብ የአዋጁን መጽደቅ በመቃወም ለኢትዮጵያ መንግስት የተቃውሞ መልዕክቶች እንዲደርሱት በማድረግ ላይ መሆናቸውም ታውቋል።

በጉዳዩ ዙሪያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አስተዳደርን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።