ጥር 18 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በስደት የሚገኘው ኢነጋማ፦”በጠመንጃ አስገዳጅነት የእውነት እጆች ቢታሰሩም፤ ታሪክና ህዝብ ግን ይፈርዳል” በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ ፤በኢትዮጵያ ውስጥ ነጻ የሆነ አስተሳሰብ እንዲነግስ፤ በተለይ የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ታላቁን ሚና መጫዎታቸውን እንዲሁም፤ ሃሳብን በነጻነት መግለጽ ፤ተፈጥሯዊና በኢትዮጵያዊያን የትግል ውጤት የተገኘ እንጂ፤ የኢህአዴግ ችሮታና ስጦታ እንዳልሆነ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ማሰማታቸውን አስታውሷል
አልፎ ተርፎም ስልጣን ከጠመንጃ ውስጥ በሚወጣ ጥይት ሳይሆን፤ ከምርጫ ሳጥን በሚገኝ የህዝብ ድምፅ መገኘት እንዳለበት በብዕራቸው ጫፍ መመስከራቸውንና ማስተማራቸውን የጠቀሰው ኢነጋማ፤ ይህን መሰረታዊ አስተሳሰብ መመሪያው አድርጎ ወደፊት የሚገሰግስ ህብረተሰብ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በመፈጠሩ፤ ለነጻነት የሚደረገው ትግል ወደፊት እንጂ ወደ ኋላ የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቁሟል።
“ላለፉት ሃያ አመታት የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞች ከፋፋይ የሆነውን የኢህአዴግ ዘረኛ አስተዳደር በማውገዛቸው፤ ለህዝብ ያላቸውን ወገንተኝነት አረጋገጡ እንጂ፤ የአገራቸውን ጥቅም በግል ጥቅም የቀየሩበት አጋጣሚ ከቶም የለም” የሚለው መግለጫው፤ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፤ በስልጣን ላይ የሚገኘው አስተዳደር፤ ጋዜጠኞችን በአገር ክህደት፣ በዘር ማጥፋት፣ ህዝብን በመንግስት ላይ በማነሳሳትና በሽብርተኝነት እየፈረጀ ለእስር፣ ለእንግልትና ለስደት መዳረጉን ይህ ትውልድ የሚመሰክረው ሃቅ ነው” ብሏል
በ’ርግጥ ጋዜጠኞች፤ የገዢዎችን ጭንብል አውልቀው አጋልጠዋል፤ ከሃገር ጀርባ የሚፈጽሙትን ደባዎች አውግዘዋል። ይህ የእውነት ነበልባል የፈጃቸውና የሃቅ ብዕር ያቃጠላቸው አምባገነን ገዢዎች ግን እንቅልፍ የነሷቸውን የብዕር አርበኞች በሰበብ ባስባቡ ማሰር፣ ማንገላታት እና ከአገር እንዲወጡ ማድረግ ተቀዳሚ ተግባራቸውና ዋነኛ አማራጫቸው አድርገውታል-ብሏል በስደት ያለው ኢነጋማ በመግለጫው።
የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች የከፈሉትን መስዋዕትነት ለመረዳት ለሃያ አመታት የከተቧቸው ድርሳናት ምስክሮች ናቸው”ያለው ኢነጋማ፤ ለዚህ የጋዜጠኞች ውለታ የኢህአዴግ አስተዳደር ፦“አሸባሪ” የሚል ቅፅል ሰጥቷቸው በማሰር፤ እውነት የሚናገሩ የፕሬስ ትሩፋቶችን ለማጥፋት የሞት ሽረት ግብግብ ላይ ይገኛል”ብሏል።
“ስለሆነም በሃሰት ክስ፣ በይስሙላ ፍርድ ቤት፣ ለሆዳቸው ባደሩ ዳኞችና ታጣቂዎች እየተመሩ እውነትን ለመግደል ዛሬም ያለመታከት እየሰሩ ያሉትን ወገኖች አንድ ነገር ልናስታውሳቸው እንወዳለን”ያለው ኢነጋማ፤” ወርቅ በእሳት እንደሚፈተነው ሁሉ፤ የኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኞችም በእሳት ተፈትነዋል። በዚህም የእሳት ፈተና እንደጨርቅ አልነደዱም፤ እንደወርቅ አንጸባረቁ እንጂ። እነሆ በህዝብ ላይ የሚደርሰውን የግፍ በትር ተጋሩ፤ መራር የሆነውን የመከራ ፅዋም ስለህዝብ ብለው ተጎነጩ። እነሱ ታሰሩ፤ እነሱ ተሰደዱ፤ ተንገላቱም። ሃሳብን በነጻነት ለመግለጽ የሚደረገው ትግል ግን፤ ከቶውኑም አይቋረጥም”ብሏል።
“እነ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ እና ርዕዮት አለሙ በሃሰት ክስ “አሸባሪ” ተብለው ለእስር ቤት ቢዳረጉም፤ መላው ህዝብ እውነተኛ ማንነታቸውን ስለሚያውቀው፤ ነጻ ጋዜጠኞቻችን ከታሰሩበት የጨለማ ክፍሎች ውጪ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው ምን ጊዜም አብረዋቸው ይቆማሉ” ሲልም ብዙሀኑ ህዝብ ዛሬም በመንፈስ ከሀቅ አርበኞቹ ጎን መሆኑን አውስቷል-ኢነጋማ።
ኢነጋማ አያይዞም፦”እንደሌሎች የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ሁሉ፤ እነሱም በእሳት የተፈተኑ ወርቆች በመሆናቸው፤ ህዝብ ታላቅ የኢትዮጵያዊነት ኒሻን ያጎናጽፋቸዋል። ከ’ንግዲህ ታሪክ እና ትውልድ የአምባገነኖችን ክፋት ሲያነሳ፤ በመሰዊያው ገበታ ላይ የቀረቡ የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞችን ግን ከፍ አድርጎ በክብር ይዘክራቸዋል። ዛሬ በህግ ሽፋን ሃቅ የሚናገሩ አንደበቶች ቢዘጉም፣ በጠመንጃ አስገዳጅነት የእውነት እጆች ቢታሰሩም፤ ታሪክና ህዝብ ግን ይፈርዳል”ብሏል።
ካለፉት ሃያ የነጻነት ትግል አመታት እንደተማርነው፤ ኢህአዴግ የተሸነፈ ሲመስለው ህዝባዊ ንቅናቄዎችን ለመግታት ሲል ፍትህን ያዛባል፤ እጁን በደም ይነክራል። አሁንም በብዕር አርበኞች ላይ የወሰደው እርምጃ ሽንፈቱን እንጂ፤ መሪነቱን አያሳይም”የሚለው የ ኢነጋማ መግለጫ፤ “ በጠመንጃ አገዛዝ እና በህግ ሽፋን፣ በኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ላይ ያደረሰውና እያደረሰ ያለው መከራም ተሸናፊነቱን ይበልጥ አጉልቶ እንደሚያሳይ አመልክቷል።
“ኢህአዴግ የግፍ እና የበደል በትሩን ባበዛው ቁጥር፤ የነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞችንና የኢትዮጵያን ህዝብ የድል ነጥብ ከፍ ያደርገዋል። ይህ ፋይዳ ቢስ ክስ እና የሚሰጠውም ፍርድ አምባገነኖች በሽብር ቆፈን ውስጥ ለመሆናቸው ጉልህ ምስክር ነው”ያለው ኢነጋማ፤” እነሆ ኢህአዴግ በፍርሃትና በሽብር ውቅያኖስ ላይ ሲቀዝፍ፤ በነጻ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተው ህዝባዊ መነቃቃት ደግሞ፤ የማያቋርጥ የጥሪ ደወሉን ከዳር እስከዳር እያስተጋባ፤ የነጻነት ትግሉን ይቀጥላል። ለዚህም ህዝቡ ከኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ጎን በመቆም፤ የአንድነት ቃል ኪዳኑን እንዲያድስ ጥሪያችንን እናቀርባለን”ሲል መግለጫውን ቋጭቷል።
ዓለማቀፉ የጋዜጠኞች ፌዴሬሽንን(አይፌክስን)እና ኦል አፍሪካን ጨምሮ ይህ የኢነጋማ መግለጫ በተለያዩ ዓለማቀፍ መድረኮች ሽፋን አግኝቷል።