መድረክ የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 በማን አለብኝነት የዜጎችን ንብረት የማፍራት የመሸጥ የመለወጥ እና የመጠቀም መብትን የገፈፈ ነው አለ

ጥር 18 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ የዜጎች የንብረት ባለቤትነት መብት ይከበር በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ ፣ ለስልጣን ማራዘሚያ ተብሎ የወጣው አዋጅ በህገ መንግስት አንቀጽ ስምንት ንኡስ አንቀጽ 3 የኢትዮጵያ ብሄሮች ፣ ብሄረሰቦችና እና ህዝቦች ሉአላዊነታቸው የሚገለጠው በዚህ ህገመንግስት መሰረት በሚመርጣቸው ተወካዮቻቸው እና በቀጥታ በሚያደርጉት ዲሞክራሲያዊ ተስፎ ይሆናል ቢልም ጉዳዩ የሚመለከተው ህዝብ በነጻነትና በግልጽነት አልተወያየበትም፤ እንዲሁም የፓርላማ አባላቱ እንዳይወያዩበት ለማድረግ የአዋጁ ረቂቅ ማታ ከምሽቱ 12 ሰአት ታድሎ ጧት 3 ሰአት ላይ እንዲጸድቅ ተደርጓል ብሎአል።

መድረክ አክሎም በደርግ ጊዜ የከተማ ቦታንና ትርፍ ቤትን  የመንግስት ንብረት ለማድረግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 47/67 ላይ “አንድ ቤተሰብ ወይም ግለሰብ ለመኖሪያ ቤት መስሪያ የሚያውለው እስከ 500 ካሬ ሜትር የሚደርስ የከተማ ቦታ ሚኒሰትሩ በሚያወጣው መመሪያ መሰረት ሊሰጥ ይችላል። እንዲሁም “አንድ ቤተሰብ ግለሰብ ወይም ድርጅት በከተማ ቤቱ የመጠቀም ወይም ይህንኑ ቤት የማውረስ የመሸጥ ወይም የመለወጥ መብት አለው ” እያለ፣ በኢህአዴግ አዲሱ የመሬት አዋጅ ግን ነባር ባለይዞታዎች መሬታቸውን በሊዝ እንዲገዙ ያስገድዳቸዋል ብሎአል።

አዲሱ አዋጅ የዜጎችን ሁሉ ተስፋ ያጨለመ፣ የአገሪቱን ህዝብ ከይዞታው ባለቤትነት አሽቀንጥሮ ጥሎ መንግስትን የመሬት ባለቤትነት ፣ ህዝብን ደግሞ ጭሰኛ የሚያደርግ ነው የሚለው መድረክ፣ ህዝብ በተለያዩ መድረኮች ቁጣውን እየገለጠ ፣ የማስጠንቀቂያ ደወሉንም እየደወለ ነው ብሎአል።

መድረክ የህዝብን እምነትና ፍላጎት በጡንቻ እየጨፈለቁ የህዝብን ጩኸት እንደ ቁራ ጩኸት እየቆጠሩ መጓዝ ለማንም አይጠቅምም የሚለው መድረክ፣ አሁን ደግሞ በአራት አመት ጊዜ ውስጥ ነባር ባለይዞታዎች መሬታቸውን ያለሊዝ እንዲሸጡ ለማስገደድ የአፈጻጸም ዝርዝር መመሪያ በአራት አመት ውስጥ ይወጣል ተብሎ መነገሩ “ዶሮን ሲያታልሉዋት አይነት ነው ብሎአል።

በመጨረሻም መድረክ በገጠር ነዋሪው አርሶ አደር ዬኢዞታው ባለቤትነት መሆን እንዳለበትና የከተማ ነዋሪውም የመኖሪያ ቤት የሰራበት መሬት ባለቤትነት እንዲረጋገጥ ፣ አዋጆችንና ድርጊቶችን ለመቃወም በምናደርገው እንቅስቃሴ መላው ህኢባችን ከጎናችን እንዲቆም እንጠይቃለን ብሎአል።

የኢትዮጵያ ህዝብ አዲሱን የመሬት አዋጅ በእየአቅጣጫው እየተቃወመው መምጣቱ የኢህአዴግን ባለስልጣናት ግራ እንዳጋባ መዘገባችን ይታወሳል።

በዚህ ዙሪያ ላይ ኢሳት ለወደፊቱ ከህግ እና ከኢኮኖሚ ባለሙያዎች ጋር ውይይት ይከፍታል።