(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 25/2010) በሕዳሴው ግድብ ላይ ለመነጋገር የኢትዮጵያ፣የግብጽና የሱዳን ባለስልጣናት ነገ በካርቱም እንደሚገናኙ ታወቀ።
በግድቡ ዙሪያ በሃገራቱ በተለይም በኢትዮጵያና በግብጽ መካከል ያለውን ልዩነት ለመፍታት በሚል የተጠራው ስብሰባ ላይ ለመገኘት የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ረቡዕ ካርቱም እንደሚገቡ ኦህራም ኦንላይን ዘግቧል።
ባለስልጣኑም የስብሰባው አላማ ውዝግቡን ለመቋጨት እንደሆነም አስገንዝበዋል።
በካርቱም ነገ በሚካሄደው ስብሰባ የየሃገራቱ የውጭ ጉዳይና የውሃ ሚኒስትሮች እንዲሁም የደህንነት ባለስልጣናት የሚገኙበት መሆኑም ተመልክቷል።
ለየካቲት ታቅዶ የነበረው ይህ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በድንገት ስልጣን በመልቀቃቸው በኢትዮጵያ ጥያቄ መራዘሙንና አሕራም የተባለው የግብጽ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል።
የሶስቱም ሃገራት ባለስልጣናት በህዳር ወር በካይሮ መገናኘታቸውን የሚያስታውሰው ዘገባ ይህም በፈረንሳይ ኩባንያ የተደረገውን ጥናት ለማጽደቅ እንደነበር አመልክቷል።
የፈረንሳዩ ኩባንያ ግድቡ በግርጌ ሀገራት አካባቢያዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ እንዲያጠና ሃላፊነት የተሰጠው መሆኑም ታውቋል።
የዚህን ቡድን ጥናት ለማጽደቅ ሃገራቱ ባለመስማማታቸው ሌላ ዙር ስብሰባ መጠራቱም ታውቋል።
ነገ በካርቱም የሚጀመረው ስብሰባም የፈረንሳዩ ኩባንያ ባደረገው ጥናት ቅድመ ሪፖርት ላይ ለመነጋገርና ለመወሰን መሆኑንም የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አህመድ አቡ ዛይድ ለመገናኛ ብዙሃኑ ገልጸዋል።