መጋቢት ፪(ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ተመድ የመንግስትን ሪፖርት ዋቢ አድርጎ ባወጣው መግለጫ ዘንድሮ በኢትዮጰያ 2.9 ሚሊዮን ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ብሏል።
ከተረጅዎቹ መካከል 38 በመቶው ከኦሮሚያ፣ 31 ከመቶው ደግሞ ከሶማሌ፣ 12 በመቶው ከትግራይ እና 6 በመቶው ካማራ ክልሎች መሆናቸውን ሪፖርቱ ያመለክታል። ለተረጅዎቹ ድጋፍ ለማድረግ 386 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ያመለከተው ተመድ፤ ይሁንና የረድኤት ድርጅቶች የፈንድ እጥረት እንዳለባቸው በመግለጽ ላይ መሆናቸውን ጠቁሟል።
በተያያዘ ዜና የጋምቤላ ክልል ባለስልጣናት ከጋምቤላ ከተማ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ቦታ <<ጄዊ>> የተሰኘ አዲስ ካምፕ ማዘጋጀታቸውን የጠቀሰው ተመድ፤ 50 ሺህ ሰዎችን የመያዝ አቅም ይኖረዋል የተባለው ይህ ካምፕ ስደተኞች ወደ ማምረት ስራ እንዲገቡ የሚያመች እንደሆነ ቅኝት ለማድረግ ወደ ስፍራው ተንቀሳቅሰው የነበሩ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሺነር ቡድን አባላትን በመጥቀስ ገልጿል።
አዲሱን ካምፕ ለማሳደግና ለማስፋፋት የኮሚሺኑ ተጨማሪ 16.5 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው በሪፖርቱ ተመልክቷል። ተመድ የመንግስትን ሪፖርት ተንተርሶ ዘንድሮ በኢትዮጰያ 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሰዎች አስቸኴይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ያወጣውን ሪፖርት እንደማይቀበሉት ኢሳት ያነጋገራቸው አንድ የረድኤት ድርጅት ሰራተኛ ተናግረዋል።
“በተመድ ስም ወጣ እንጂ ሪፖርቱ የመንግስት ነው” ያሉት የረድኤት ሰራተኛው፤ ደሀ መንግስታት ደግሞ ሁሌ የፖለቲካ ጨዋታቸው እንዳይበላሽ ሲሉ የተረጅዎችን ቁጥር መቀነስ ልማዳቸው ነው” ብለዋል።
አስተያየታቸውን ሲያጠቃልሉም፤ቅኝቱና ጥናቱ በገለልተኛ ወገኖች፣ በተመድ ሰራተኞች አለያም በረድኤት ድርጅት ወኪሎች ቢደረግ ኖሮ የተረጅዎች አሀዝ አሁን ከተጠቀሰው በእጥፍ ይጨምር እንደነበር ተናግረዋል።