የጠቅላይ ሚኒስትሩ የትውልድ መንደር  ነዋሪዎች በውሀ፣ በመብራትና በስልክ ችግር ክፉኛ እያማረሩ ነው።

መጋቢት ፪(ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ነዋሪዎቹ  ምሬታቸውን ለኢሳት ሲግልጹ፦” አቶ ሀይለማርያምን  ከልባችን አውጥተን ከጣልነው ቆይተናል” ብለዋል።

በደቡብ ክልል በወላይታ ዞን   የጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ የትውልድ ቦታ የሆነችው  የአረካ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት  በጠቅላላ የወላይታ ዞን  ነዋሪዎች በውሀ፣በመብራትና በስልክ ችግር  መማረር ከጀመሩ ረዥም ጊዜያት ሆኗቸዋል።

በተለይ ካለፉት ሁለት ወራት  ወዲህ የአቶ ሀይለማርያም የትውልድ መንደር በሆነችው  በአረካ አገልግሎቱ ጠቅላላ የቆመበት ደረጃ ላይ መድረሱን የተናገሩት ነዋሪዎቹ፤ በዚህም ሳቢያ  አንድ ጀሪካን ውሀ እስከ 15 ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑን  ጠቁመዋል።

የወረዳው ብቻ ሳይሆን  በአጠቃላይ የዞኑ ህዝብ  ጠቅላይ ሚኒስትሩን  እየረገመና እያወገዘ እንደሚገኝ የተናገሩት ነዋሪዎቹ፤ “እንዲህ የቀለዱብን ብንመርጣቸውም፣ባንመርጣቸውም ኮሮጆ የመገልበጥ  ልምዱን ስለተካኑበት ነው” ብለዋል።

“ህዝቡ እጅግ ተማርሯል፤ ወደ ጨለማ ዘመን እየተመለስን ነው፣ ምን እናድርግ? ብሶታችንን ለማን እንናገር?” ያሉት ነዋሪዎቹ፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ተስፋ አድርገን የነበረ ቢሆንም፤ ገዥው ፓርቲ በሆነ ባልሆነው ሰበብ እየፈለገ እያጠፋቸው ነው።”ብለዋል።

ችግሮቹን አስመልክተው ለሚመለከታቸው አካላት በተደጋጋሚ አቤቱታ ቢያቀርቡም ምንም ዓይነት ተግባራዊ ምላሽ ሊያገኙ አለመቻላቸውን የተናገሩት  የአርኪያ ነዋሪዎች፤ “ወዴት እንሂድ?”ሲሉ  ምሬታቸውን ገልጸዋል።