(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 22/2010) በመላው አለም በሚገኙ 50 ከተሞች የተዘጋጀው የኢሳት 8ኛ አመት በአል በተሳካ ሁኔታ ተካሄደ።
በአሜሪካ፣አውሮፓ፣በውስትራሊያእንዲሁም በሩቅ ምስራቅና በመካከለኛው ምስራቅ በአንድ ቀን የተዘጋጀው የኢሳት 8ኛ አመት ክብረ በአል በርካታ እንግዶች በታደሙበት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁም ተመልክቷል።
የኢሳት ሶስት ስቱዲዮዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በቀረበበት እንዲሁም የኢሳት 8 አመታት ጉዞ በዘጋቢ ፊልም በቀረበበት በዚህ ዝግጅት ስነ ስርአት ላይ የታደሙት እንግዶች ኢሳት በደረሰበት ደረጃ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በየከተሞቹ የስነስርአቱ ታዳሚዎች የሆኑ በቀጥታ የተሳተፉበት ይህ ዝግጀት ውጤታማ መሆኑም ተመልክቷል ።የኢሳት የኦፕሬሽን ክፍል ሃላፊና የዝግጅቱ ዋና አስተባባሪ አቶ ግሩም ይልማ እንደገለጸው በአንዳንድ ከተሞች ላይ ካጋጠሙ ቴክኒካዊ ችግሮች በስተቀር ዝግጅቱ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።
የበአሉ ታዳሚዎች በቀጥታ ስርጭቱ ላቀረቡት ጥያቄም በኢሳት ስቱዲዮ የቀጥታ ስርጭት ላይ ምላሽ ተሰጥቷል።
በኢሳት በኩል ደካማ ጎኖች እየተቀረፉ ጠንካራ ጎኖቹ እየጎለበቱ እንዲሄዱና በዚሁም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከታዳሚዎቹ ምክርና አስተያየት ተሰጥቷል።
የኢሳት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ በዝግጅቱ የተሳተፉት ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውንም የኢሳት የኦፕሬሽን ክፍል ሃላፊና የዝግጅቱ ዋና አስተባባሪ አቶ ግሩም ይልማ ገልጿል።
በሰሜን አሜሪካና አውሮፓ ከተሞች ብሎም በአውስትራሊያ እንዲሁም በሩቅ ምስራቅ ኮሪያ፣በመካከለኛው ምስራቅ እስራኤል እኒሁምበኒውዝላንድ ከተሞች በአጠቃላይ በ50 ከተሞች የተዘጋጀውና በቀጥታ ሁሉንም በአንድ ቀን ለማገናኘት የተቻለበት ሒደት የኢሳት ቴክኒካዊ ብቃት የታየበት እንደሆነም በአንዳንድ ተሰብሳቢዎች ምስክርነት ተሰጥቶበታል።
የኢሳት 8ኛ አመት በአንድ ቀን በጋራ በ50 ከተሞች ቢዘጋጅም በየከተሞቹ በተናጠል የሚከበረው የ8ኛ አመት ክብረ በአልም እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል።