የኢህአዴግ ፍ/ቤት በህመም የሚሰቃየው ሃብታሙ አያሌው ውጭ አገር እንዲታከም ዕግድ አላነሳም

ኢሳት (ሰኔ 28 ፥ 2008)

ለሳምንታት ከፍተኛ የህመም ስቃይ ላይ የሚገኘው ሃብታሙ አያሌው የውጭ ሃገር ህክምና እንደሚያስፈልገው በሃኪሞች ማረጋገጫ ቢሰጠውም ፍርድ ቤቱ ዕግድን እስካሁን አላነሳም። የሃኪም ማስረጃውን አይቶ ዕግድን ለማንሳት የተሰየመው ችሎት አልተሟላም በሚል ያለቀጠሮ መነሳቱንም ከአዲስ አበባ የደረሰን ዜና ያስረዳል።

የአንድነት ፓርቲ አመራር የነበረውና ከሃብታሙ ጋር በወህኒ ቤት እስር ላይ ቆይቶ የተለቀቀው ዳንዔል ሺበሺ ለኢሳት እንደተናገረው የውጭ ሃገር ህክምና እንደሚያስፈልገው የሚያሳየው ሰነድ ሰኞ ዕለት ፅ/ቤቱ የቀረበ ሲሆን፣ ማክሰኞ ዕለት ፍ/ቤቱ ውሳኔ እንደሚሰጥ በመጠበቁ በርካታ የሃብታሙ የትግል አጋሮች ቤተሰቦቹና ወዳጆቹ በችሎቱ ተገኝተዋል።

ችሎቱ ሳይሟላ በሁለት ዳኛ ብቻ ከተሰየመ በኋላ፣ ዳኞች አልተሟሉም የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸዋል። በችሎቱ ያልተገኙትና ለዳኞች አለመሟላት ምክንያት የሆኑት ሰብሳቢው ዳኛ አቶ ዳኜ መላኩ፣ በግቢው ውስጥ እንደነበሩና እርሱን ጨምሮ ብዙ ሰዎች እንዳዩአቸው ለኢሳት በሰጠው ቃለምልልስ አስረድተዋል።

ሰብሳቢው ዳኛ የሆኑትና ለችሎቱ መጓደል ምክንያት የሆኑት አቶ ዳኜ መላኩ ከሳምንት በፊት የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚደንትና ሹመት እንደተሰጣቸው ይታወሳል።

ያለሰብሳቢው ዳኛ የተሰየመው ችሎት በሃብታሙ የህክምና ሪፖርት ላይ ውሳኔም ቀጠሮም ሳይሰጥ ተመልሳችሁ በጽ/ቤት በኩል ተከታተሉ የሚል ምላሽ ሰጥቷል። በዚሁ የፍ/ቤቱ ውሳኔ የተደናገጠችው የሃብታሙ አያሌው ባለቤት ራስዋን ስታ መውደቋን በኋላም ወደ ድንገተኛ የህክምና ክፍል መወሰድዋን ከዳንኤል ሺበሺ ቃለምልልስ መረዳት ተችሏል። ሆኖም ህክምና ከተከታተለች በኋላ ነቅታ በመልካም ጤና ላይ መሆንዋ ታውቋል።