የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ቢሮ ለሁለት የኢሳት ባልደርቦች በቤተሰቦቻቸው በኩል ማስጠንቀቂያ ላከ

ኢሳት (ሰኔ 28 ፥ 2008)

በአቶ ጌታቸው አሰፋ የሚመራው የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ቢሮ ለሁለት የኢሳት ባልደርቦች በቤተሰቦቻቸው በኩል ማስጠንቀቂያ ላከ። የደህንነት አባላቱ ኢትዮጵያ በሚገኙት የጋዜጠኞቹ ቤተሰቦች ቤት በመሄድና በመጥራት ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

ረቡዕ ሰኔ 22 ቀን 2008 ዓም በተመሳሳይ ቀን በሃገሪቱ የደህንነት መስሪያ ቤት ሰራተኞች በኩል ማሳሰቢያው የደረሳቸው የኢሳት ባልደርቦች ታማኝ በየነና ሲሳይ አጌና በጋራ በጻፉት ደብዳቤ መልዕክቱ እንደደረሳቸው ገልጸው፣ ማናቸውም መደለያና ማስፈራሪያ ከተነሱበት ዓላማ እንደማያቆማቸው አረጋግጠዋል።

አርቲስና አክቲቪስት ታማኝ በየነና ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና በአድራሻ ለደህንነት ዋና ሃላፊው ለአቶ ጌታቸው አሰፋ ሰኔ 27/2008 (July 4, 2016) በጻፉት ደብዳቤ “በሃገራችን በነጻነት መኖር ወይንም ሃገራችንን በነጻነት ማየት ባለመቻላችን በሰው ሃገር በነጻነት እየኖርን፣ ነጻነታችንን ለማስመለስ በጥቅል ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያንም በነጻነት እንዲኖሩ የአቅማቸውን ጥረት ከሚያደርጉት ውስጥ እንገኛለን” ካሉ በኋላ “ጥረታችን በርሰዎ መስሪያ ቤትም ሆነ በሕወሀት መንግስት እንደማይወደድ የምናውቅ ቢሆንም ማስፈራሪያና መደለያ በማቅረብ ትደፍሩናላችሁ የሚል ግምት አልነበረንም” በማለት ለህወሃት መሪዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመቀጠልም፣ “እናንተ በደል አንገፈገፈን ብላችሁ ለመብታችሁ እሰከመጨረሻው ታግላቹኋል።እናንተ በተራችሁ በበደል ላይ በደል ስትጭኑብን ፡ኢትዮጵያን በዘረኝነት ስትቀጠቅጡና ስትዘርፉ ይህንን በዝምታ እንድንመለከት ማስፈራሪያ መላካችሁ የሚያናድድ ቢሆንም ይህ ድፍረት ይበልጥ ጉልበት እንደሰጠን ለርስዎም ሆነ የትኛው የሕወሓት ቡድን እንደሚመራው በውል ላልታወቀው መንግስትዎ ማስታወስ እንሻለን። ማናቸውም ማሰፈራሪያና መደለያ እንዲሁም ቤተሰቦቻችንን በዕገታ በመያዝ ከነጻነት ጉዞ አንዲት ስንዝር እንደማትመልሱን እናረጋግጣለን” ሲሉ እያደረጉ ካሉት የነጻነት ትግል ምንም ነገር እንደማይበግራቸው አስታውቀዋል።