ኢህአዴግ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን እያሳደደ ማሰሩን ቀጥሏል

የካቲት 21 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአጭር ጊዜ ውስጥ ራሱን እያጠናከረ የመጣው  የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/ኢሶዴፓ/፤ከወዲሁ የማዳከምና የማፍረስ ዘመቻ እንደተከፈተበት፤ ፍኖተ ነጻነት ዘግቧል።

ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ መድረክ ጽ/ቤት የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በአሁኑ ጊዜ የኢሶዴፓ አመራሮች በየቦታው እየታሰሩ ናቸው።

መድረክ እንዳለው፤የኢሶዴፓ የዳውሮ ተጠሪ የሆኑት አቶ ታዬ ወ/ማሪያም በፈጠራ ክስ ተከሰው ሁለት ዓመት ተፈረዶባቸው ማረሚያ ቤት የገቡ ሲሆን፤ በጋሞጐፋ ዞን የከምባ ወረዳ ተጠሪ የሆኑት አቶ ህዝቄልም  በሐሰት ክስ  ሦስት ወር እስራት ተፈርዶባቸው ታስረዋል።

በተለያዩ አካባቢዎችም በፓርቲው አባላት ላይ  እስራትና ወከባ እየተፈፀመባቸው እንደሆነ ተዘግቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በፈጠራ የሽብርተኝነት ክስ 20 ዓመት የተፈረደባቸው አቶ ዘሪሁን ገብረ እግዚአብሔርና 14 ዓመት የተፈረደበት ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፤ለበላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ እንደማይጠይቁ ታውቋል።

አቶ ዘሪሁንና ጋዜጠኛ ውብሸት ይግባኝ የማይጠይቁት፤ በፍትህ ሥርዓቱ ላይ እምነት በማጣታቸውና- የበላይ ፍርድ ቤቱም ቀደም ሲል ክሳቸውን ሲያስችል ከቆየው ፍርድ ቤት  የተለዬ ውሳኔ ውሳኔ ያሳልፋል ብለው ስለማያምኑ ነው።

 በተያያዘ ዜናም አንድነት ፓርቲ በቀጣይ ትግሉ፤ ከጋዜጣዊ መግለጫ በዘለለ ሁሉንም ዓይነት የሰላማዊ ትግል ስልቶች ለመጠቀም ውሳኔ አሳለፈ።

የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ይህን ውሳኔ ያሳለፈው፤ የአቶ አንዷለም አራጌን  በእስር ቤት መደብደብ ተከትሎ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ነው።

“በህዝባዊ ንቅናቄ ሰላማዊ ትግል ያሸንፋል”በሚል ርዕስ ፓርቲው ባወጣው መግለጫ፤በ ኢህአዴግ መንግስት በሁሉም አቅጣጫ እየተፈፀሙ ያሉት በደሎችና ግፎች ከ አቅም በላይ እየሆኑ በመምጣታቸው፤ሰላማዊ የትግል ስልቶችን በሙሉ በመጠቀም እስከመጨረሻው በቁርጠኝነት ለመታገል መወሰኑን አስታውቋል።

አቶ አንዷለም አራጌ በተለይ ጭንቅላቱ ላይ  በደረሰበት ድብደባ ሚዛኑን ጠብቆ መቆም ተስኖት ከቤተሰቦቹ ጋር የሚነጋገረው በጠባቂዎች እየተደገፈ  መሆኑ፤በ ፓርቲው አመራሮችና በቤተሰቦቹ ዘንድ በጭንቅላቱ ውስጥ ደም ሳይፈሰው አልቀረም የሚል ከፍ ያለ ስጋት ፈጥሯል።

 ይሁንና፤ የተሻለ ህክምና እንዲያገኝ ያቀረበው ጥያቄ እስካሁን ድረስ ተቀባይነት አላገኘም።

“በፓርቲያችን ከፍተኛ የአመራር አባል በአቶ አንዱዓለም አራጌ ላይ የተፈፀመው የድብዳባ ወንጀል፤ ግልጽ የሆነ የፖለቲካ ጥቃት ነው ብለን እናምናለን”ያለው አንድነት፤ ይህ ወንጀልና ኢ-ሠብአዊ የእስረኞች አያያዝ ፤ገለልተኛ በሆነ አካል እንዲጣራና ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ አሣስቧል።

እንዲሁም አቶ አንዱዓለም አራጌም በሚመርጡት የግል ሃኪም እንዲታዩ እና መንግሥት ለተግባራዊነቱ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አንድነት ጠይቋል።

አንድነት ፓርቲ በጉዳዩ ዙሪያ መክሮ የትግል አቅጣጫውን ለመተለም በጠራው በዚሁ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ፤ በርካታ የፕርቲው አመራሮች  በአቶ አንዷለም ላይ በሆነው ነገር ሀዘንና ቁጭታቸውን ሲገልጹ ተደምጠዋል-“ታስረንም፤እንደበደባለን”በማለት።

 አንድነት፤ በስብሰባው መጠናቀቂያ ባወጣው የአቋም መግለጫ፦  “የፓርቲያችን ቀጣይ የትግል እንቅስቃሴ ከጋዜጣዊ መግለጫ በዘለለ ወደ ህዝቡ ለመዝለቅ ሁሉንም አይነት የሠላማዊ ትግል ሥልቶችን እንዲጠቀም ብሔራዊ ምክር ቤቱ ወስኖ መመሪያ ሰጥቷል”ብሏል።

እንዲሁም፦”ወቅቱ በእጅጉ የፖለቲካ ምህዳሩ እየጠበበ የመጣበት በመሆኑ ለህግ የበላይነት መረጋገጥ በጋራ ለመታገልና ትግሉን ወደ ህዝብ ለማዝለቅ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የአብሮነት እንቅስቃሴ ወሳኝ በመሆኑ ለሠላማዊ ትግሉ በጋራ እንዲቆሙ”ሲል አንድነት ለሌሎች ፓርቲዎችም የጋራ የትግል ጥሪ አቅርቧል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide