ታኀሳስ ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰሞኑን በኦሮምያ ተከስቶ የነበረውን ህዝባዊ ተቃውሞ አስመልክቶ ከሁሉም የኢህአዴግ ድርጅቶች የተውጣጡ ካድሬዎች ሃረር ላይ ባደረጉት ስብሰባ ድርጅታችን ከህዝብ ጋር ተለያይቷል በማለት እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።
ካድሬዎቹ “ኢህአዴግ ውስጡ ተበላሽቷል፣ ራሱን ይመርምር ብለዋል።” በሌላ በኩል የኦሮሞ ሕዝብ አዲስአበባና የኦሮሚያ ዙሪያ ከተሞች የጋራ ማስተር ፕላኑ ሕይወቴ ከተመሠረተበት መሬት አፈናቅሎ ለጭሰኝነትና ለልመና ይዳርገኛል በሚል የጀመረው ተቃውሞ ሰላማዊና ሕጋዊም እንደነበር እንደሚያምኑ ነገርግን መንግስት ሕዝባዊ ተቃውሞን በሃይል ለመመለስ በመሞከሩ ሕዝቡን ወደቁጣ ወስዶት ለንብረትና ለሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑን ዘጋቢያችን ያነጋገርናቸው አዲስአበባ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
ይህንን ተከትሎ ማስተር ፕላኑን የተቃወሙ ሰዎችን ግንቦት 7 እና ኦነግ ብሎ በመፈረጅ በዘመቻ መልክ ማሰር መጀመሩ እንዳሳዘናቸው፣ ይህም ሁኔታ ይበልጥ ከሕዝብ ጋር መቃቃርን ከመፍጠር የዘለለ ውጤት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡
የማስተር ፕላኑ ጉዳይ ከአንድ ዓመት ተኩል ጀምሮ ደም አፋሳሽ በሆነ መልኩ ተቃውሞ እንደቀረበበት የጠቀሱት ሌላኛው አስተያየት ሰጪ፣ ነገር ግን መንግስት ፕላኑን ከሕዝብ ፍላጎት ውጪ ለመተግበር ባለው ፍላጎት ምክንያት እንደገና ግጭት ቀስቃሽ ድርጊት መፈጸሙ በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለው እኩይ ድርጊት ነው ሲሉ ተቃውመውታል፡፡
ኢህአዴግ ከማስተር ፕላኑ ጋር ተያይዞ የተነሳውን ሕዝባዊ ቁጣ በጥይት በእንጭጩ ለመቅጨት የተጠቀመበት ዘዴ ባለመስራቱ ምክንያት በበርካታ ከተሞች ተቃውሞ ተስፋፍቶ መሰንበቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ተቃውሞው ጋብ ካለ በሃላ የሚጠረጥራቸውን ሁሉ ወደማሰር ዘመቻ መግባቱ በኦሮሞዎች ብቻ ሳይሆን በሌላውም የህብረተሰብ ክፍል ሲወገዝ ሰንብቶአል፡፡
በተለይ በአዲስአበባ በአንዳንድ ወረዳዎች በተደረጉ ስብሰባዎች ላይ ሕዝቡ በግልጽ የመንግስትን የሃይል እርምጃ ማውገዙ የኢህአዴግን ከፍተኛ ካድሬዎች ያስደነገጠ ጉዳይ ሆኖአል፡፡