በባህር ዳር ከተማ የሚታየው የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ነዋሪውን አስመርሯል

ታኀሳስ ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከክረምቱ መግባት ጀምሮ በከተማዋ በተደጋጋሚ የሚታየው የመብራት መቆራረጥ ነዋሪውን ያስመረረ ሲሆን፣ በአስቸኳይ ጥገና መስክ የተሰማሩት ሰራተኞች የሚጠቀሙበት መኪና ከአስርት አመታት በፊት የነበረ አሮጌ ከመሆኑም በላይ በቁጥርም አንድ ብቻ መሆኑ ስራውን እንዳወሳሰበው ባለሙያዎቹ ተናግረዋል፡፡
የደንበኞች ቁጥር እየበዛ በሄደ ቁጥር ያሉት ገመዶች የኤሌክትሪክ ኃይሉን መሸከም ባለመቻላቸው መቀየር ሲገባቸው ለረዥም ዓመታት ባሉት ገመዶች የመጠቀሙ አሰራር መቀጠል አንዱ ችግር ፈጣሪ መሆኑን ገልጸዋልል፡፡መስመሮች ከትራንስፎርመሩ እየራቁ በሄዱ ቁጥር የኤሌክትሪክ ኃይል እየደከመ እንደሚሄድ የሚናገሩት ባለሙያ በእያንዳንዱ ትራንስፎርመር መጠባበቂያ ኃይል ባለመያዙ የኃይል መቆራረጥ ችግሩ በየጊዜው ለመታየቱ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል በአንድ አካባቢ ሲቋረጥ ኮርፖሬሽኑ በሁለት ሰአት ውስጥ ምላሽ መስጠት እንዳለበት በመስሪያ ቤቱ ደንብ ላይ የሰፈረ ቢሆንም አሁን ግን መብራት ጠፍቶባቸው ለቀናት የሚቆዩ ደንበኞች አየተበራከቱ መምጣታቸው የቅንጅት እጥረት መሆኑን ይናገራሉ፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽኑ ከአሁን በፊት ይጠቀምበት የነበረው የመለዋወጫ ዕቃዎች ጥራታቸውን የጠበቁ በመሆናቸው ረዥም ጊዜ ያገለግሉ እንደነበረ የሚናገሩት ባለሙያ በአሁኑ ጊዜ ኮርፖሬሽኑ የሚጠቀምባቸው መለዋወጫዎች ግን የወረደ ጥራት ስላላቸው በቀላሉ በመቃጠል በህብረተሰቡ ንብረት ላይ ተደጋጋሚ አደጋ የሚያደርሱ መሆናቸውን ገልፀዋል በአስቸኳይ ጥገና ክፍል ለሚያገለግሉ ሰራተኞች አስተዳደሩ ስራቸውን በአግባቡ እንዲወጡ እገዛ ባለመደረጉ ህብረተሰቡን በተፈላጊው መጠን ማገልገል ያለመቻሉን የሚገልጹት አስተያየት ሰጪ ስራው በአግባቡ ባለመሰራቱ የህብረተሰቡን አገልግሎት ብቻ ሳይሆን የኮርፖሬሽኑን ጥቅም እንደሚያሳጣ ተናግረዋል፡፡
የኮርፖሬሽኑ ቅንጅታዊ አሰራር አለመኖር በየጊዜው የሚከሰተውን ጉድለት በአግባቡ ለመፍታት የሚያስችል አሰራር ባለመኖሩ በህብረተሰቡ ላይ ችግር ከመፈጠሩም በላይ፤ በሰራተኞች ሞራል ላይ በፈጠረው ጫና የኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች የድርጅቱን መለያ ልብስ ለመልበስ የሚያፍሩበት ደረጃ ላይ መድረሳቸው ጉዳዩ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ አካል ባለመኖሩ መሆኑን ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡