(ኢሳት ዜና–ሕዳር 1/2010)የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አመራሮች ለራሳቸው አካባቢ የማድላትና ሁሉንም ሕዝብ እኩል ያለማየት ችግር አለባቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።
አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ይህንኑ ችግር ለማስወገድ በኦሮሚያና አማራ ክልል መካከል የተካሄደው ሕዝባዊ የምክክር መድረክ በሌሎች ክልሎችም በቅርቡ ተግባራዊ ይደረጋል።
የኢህአዴግ ማዕከላዊ አሰራር ተዳክሞ አባል ድርጅቶች መርህ እየጣሱ ነው መባሉም ትክክል አይደለም ሲሉ ገልጸዋል።
አቶ አባዱላ ገመዳ በቴሌቪዥን ወጥተው ከአፈጉባኤነት ለመልቀቅ ጥያቄ ስለማቅረባቸው መግለጻቸውም ልክ አይደልም ብለዋል።
በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ልዩነት እየተፈጠረ መሆኑን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያሉ ክስተቶች ያመላክታሉ የሚሉ አስተያየቶች ሲደመጡ ቆይተዋል።
ይህም የኢሕአዴግ ማዕከላዊነት መርህ እየተጣሰ ሕወሃት ተዳክሟል የሚሉት ብዙዎች ነበሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም በሰጡት መግለጫ ግን ኢሕአዴግ መርሁ ተጥሶ አያውቅም ሲሉ ነው የገለጹት።
ይህም ሆኖ ግን ይላሉ አቶ ሃይለማርያም ሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችና አጋሮች የየትኛውም አካባቢ ሕዝብ የእኔ ነው ብሎ ያለማሰብ ችግር ነበር ብለዋል።
የጸጥታ አካላትም ሕገ መንግስቱን መጠበቅ ሲገባቸው በደምና በጎሳ ላይ የተመሰረተ አመለካከት እየያዙ በመምጣታቸው በግጭቶች ውስጥ ተሳታፊ ሆነው ተገኝተዋል ነው ያሉት።
ክልሎች ከፌደራል መንግስቱ ጠንክረው ወጥተዋል መባሉን ግን አስተባብለዋል።
በአጎራባች ክልሎች መካከል እየተካሄደ ያለው የሕዝብ ለሕዝብ ጉባኤም በፌደራል መንግስት እቅድና በእኛ እውቅና የተካሄደ ነው ብለዋል።
አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ የኦሮሞ ሕዝብን መብት ለማስከበር እታገላለሁ ማለታቸውም የዲሞክራሲ ማዕከላዊነት መጥፋቱን አያመላክትም ነው ያሉት።
ይህ ደግሞ ኢህአዴግን ሊበትነው አይችልም፣ታላቁ መሪያችን መለስ ዜናዊ በሞቱ ጊዜ እንኳን ኢሕአዴግ አልተበተነም በማለት በእርሳቸው መልቀቅ የሚያጣው ነገር እንደሌለ ገልጸዋል።
ከአፈጉባኤነት ለመልቀቅ ጥያቄ ስለማቅረባቸው በቴሌቪዥን ወጥተው መናገራቸውን ግን አግባብ አልነበረም እንደ አቶ ሃይለማርያም ገለጻ።
ሼህ መሀመድ አላሙዲን ከሙስና ጋር በተያያዘ መታሰራቸውን በተመለከተ አቶ ሃይለማርያም እንዳሉት ደግሞ ጉዳዩን አስመልክቶ በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት መረጃዎችን እያሰበሰበ ይገኛል።
በሳውዲ መንግስት ሉአላዊነት ግን ጣልቃ አንገባም ብለዋል።
በኢትዮጵያ ባለው የአላሙዲን ኢንቨስትመንት ላይ ግን የሚፈጥረው እክል አይኖርም ሲሉ በደፈናው አልፈውታል።