መጋቢት ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ሰሞኑን በተከታታይ ባካሄዱዋቸውና በመተካካት ረገድ እምብዛም ለውጥ ያልታየባቸው
ጉባዔዎች በአብዛኛው ነባር አመራሩን ይዘው ሲያስቀጥሉ መጠነኛ የሆነ እርምጃም ወስደዋል፡፡
በዚሁ መሰረት ኦህዴድ አቶ አባዱላ ገመዳን፣ ግርማ ብሩን እና ኩማ ደመቅሳን ከስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ሲያሰናብት፤ ብአዴን በበኩሉ የፍትህ ሚኒስትር የሆኑትን አቶ ብርሃን ኃይሉን፣ደኢህዴን ደግሞ አቶ ተሾመ ቶጋን አሰናብቷል፡፡
ብአዴን በጤና ችግር መደበኛ ስራቸውን ማከናወን የተሳናቸውና ነባር ታጋይ የሆኑትን አቶ ህላዊ
ዮሴፍን፣ኦህዴድ ወ/ሮ አስቴር ማሞን በኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚነት እንዲመረጡ አድርጓል፡፡በተጨማሪም ኦህዴድ
የፌዴራል ፖሊስ ኮምሽነሩን አቶ ወርቅነህ ገበየሁን የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ አባል እንዲሆኑ መርጧቸዋል፡፡
በሟቹ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዕቅድ መሰረት በመተካካት ሒደቱ እስከ 2007 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ቦታ ይለቃሉ
ተብለው ይገመቱ የነበሩት ነባር ታጋዮች ለቀጣይ ሁለት ዓመት ተኩል ጊዜያት እንዲቀጥሉ መደረጉ በተለይ ከፍተኛ
አመራሩ የመለስን ራዕይ ለማሳካት በተደጋጋሚ የገባውን ቃል ማጠፉን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ተናግረዋል፡፡
በ2003 ዓ.ም በመተካካት ስም የመንግስት ከፍተኛ ኃላፊነታቸው የለቀቁት አቶ አዲሱ ለገሰን ጨምሮ አቶ በረከት
ስምኦን፣አቶ ህላዊ ዮሴፍ፣አቶ አባይ ወልዱ እና የመሳሰሉት ስልጣናቸውን ወደማጠናከር ፊታቸውን
ማዞራቸው የመተካካት ዕቅዱ ውሃ እንደበላው ማሳያ ሆኗል፡፡ አቶ አዲሱ ከድርጅቱ በአቶ መለስ አማካኝነት ከተሰናበቱ በሁዋላ ተመልሰው መምጣታቸው አስገራሚ ሆኗል። አቶ አዲሱ ከስልጣን እንዲነሱ የተደረገው እርሳቸው ባልጠበቁበት መንገድ እንደነበር መግለጻቸው ይታወሳል።
በመተካካት ስም በ2003 የመንግስት እና ከፓርቲ ኃላፊነታቸው የለቀቁትን እነ አቶ ስዩም መስፍን ጨምሮ ሌሎች 9
የህወሃት አባላት በራሳቸው ፈቃድ በአብዛኛው ከጤና ጋር በተያያዘ ድርጅቱን ለመልቀቅ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት የተሰናበቱ ሲሆን የእነዚህ ሰዎች መልቀቅ እንደመተካካት ለማየት እየተደረገ ያለው የማደናገሪያ ፕሮፖጋንዳ አሳዛኝ መሆኑን ምንጮቻችን ተናግረዋል፡፡በራሳቸው ፈቃድ ከለቀቁት መካከል አቶ ስዩም መስፍን ፣ አቶ ብርሃነ ገብረክርስቶስ ፣ አቶ አርከበ
ዕቁባይና አቶ ዘርዓይ አስገዶም ይገኙበታል፡፡
የዘጠኝ የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በአንድ ጊዜ መልቀቂያ ማቅረባቸው አጋጣሚ ሳይሆን ከአቶ መለስ ህልፈት
በሓላ በህወሃት ውስጥ ከተፈጠረው ልዩነት ጋር በተያያዘ ሳይሆን እንደማይቀር ምንጫችን ቢጠቅስም ይህን በተመለከተ
ለማረጋገጥ ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም፡፡ ብዙዎች እንደሚገምቱት ከአቶ አርከበ እቁባይ ጋር ጤነኛ ግንኙነት ያልነበራቸው ወ/ሮ አዜብ መስፍን በዚህ ጉባኤ በድል አድራጊነት ወጥተዋል። ህወሀት የአቶ አባይ ወልዱን ባለቤት ወ/ሮ ትረፉ ኪዳነማርያምንም በስራ አስፈጻሚነት መርጧቸዋል።
ድርጅቶቹ ባካሄዱት ምርጫ መሰረት ከህወሃት፡- አቶ አባይ ወልዱ፣ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል፣ወ/ሮ አዜብ
መስፍን፣አቶ አባይ ጸሐዬ፣ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሔር፣አቶ በየነ ምክሩ፣አቶ ኪሮስ
ቢተው፣አቶ አስመላሽ ወ/ስላሴ፤ከብአዴን፡-አቶ አዲሱ ለገሰ፣አቶ በረከት ስምኦን፣አቶ አያሌው ጎበዜ፣አቶ ገዱ
አንዳርጋቸው፣አቶ ደመቀ መኮንን፣አቶ አለምነው መኮንን፣አቶ ካሳ ተ/ብርሃን፣አቶ ህላዊ ዮሴፍ፣አቶ ተፈራ
ደርበው፤ከኦህዴድ፡-አቶ አለማየሁ አቶምሳ፣አቶ ሙክታር ከድር፣ወ/ሮ አስቴር ማሞ፣አቶ ወርቅነህ ገበየሁ፣አቶ
ሶፊያን አህመድ፣አቶ ድሪባ ኩማ፣አቶ አድልቃድር ሁሴን፣አቶ ኡመር ሁሴን፣አቶ አበራ ኃይሉ፤ ከደኢህዴን፡-አቶ
ኃይለማርያም ደሳለኝ፣አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣አቶ ሬድዋን ሁሴን፣አቶ መኩሪያ ኃይሌ፣አቶ ሲራጅ ፈጌሳ፣ዶ/ር ሽፈራው
ተ/ማርያም፣አቶ አለማየሁ አሰፋ አቶ ደሴ ዳልቼ፣አቶ ተስፋዬ ቢነግዴ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ሆነው እንዲሰሩ
በየድርጅቶቻቸው ተመርጠዋል፡፡
ከፊታችን ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን እስከ 17 ቀን 2005 ዓ.ም በባህርዳር ከተማ የሚካሄደው የኢህአዴግ ጉባዔ
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን በሊቀመንበርነት፣አቶ ደመቀ መኮንን በምክትል ሊቀመንበርነት በድጋሚ ይመርጣል ተብሎ
እንደሚጠበቅ ምንጮቻን ጠቁመዋል፡፡
የኢህአዴግ ድርጅቶች ያደረጉትን ሹም ሽር በተመለከተ ጥያቄ ያቀረብንላቸው አንድ የቀድሞ የሀወሀት ነባር ታጋይ ፡ ምርጫውን “ውሀ ቢወቅጡት ነው” ብለውታል። “ከእነዚህ ሰዎች ምንም የሚጠበቅ ነገር የለም፣ ምን አዲስ ነገር እንደማይፈጥሩም ይታወቃል። የአፈና ስርአቱ እንደሚቀጥል ጥሩ ማሳያ ነው” ብለዋል ታጋዩ።