ጥር 20 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ) እንዳለው፤ ካለፈው ጥር 8 ቀን እስከ ጥር 15 ቀን ባሉት ሰባት ቀናት ውስጥ ብቻ፤ 38 የመኢአድ አባላት ታስረዋል።
ከነዚህም መካከል 21ዱ፤ የኢህአዴግ አንድ ክንፍ ከሆነው ከደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር-ደኢህዴግ አባልነት ራሳቸውን በማግለል፤ ወደ መኢአድ የገቡ ናቸው።
እንደ መኢአድ ህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ገለፃ፤ የኢህአዴግ አባላት የነበሩት 21 ሰዎች የታሰሩት፤ በመ ኢአድ አባልነት በተመዘገቡ ማግስት ነው።
የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዋን ወይዘሪት መሶበወርቅ ቅጣውን እና የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና በፓርቲው የደቡብ ቀጠና ኃላፊ አቶ እንድርያስ ኤሮን በመጥቀስ ሰንደቅ እንደዘገበው፤ 38ቱ የመኢአድ አባላት የታሰሩት ፤በጎፋ ልዩ ዞን በሦስት ወረዳዎች በሚገኙ ስድስት ቀበሌዎች ውስጥ ነው።
ወይዘሪት መሶበወርቅ እንዳሉት፤በዛላ ወረዳ ሻልዴ ቀበሌ ውስጥ ከጥር 9 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ አቶ ወሪዳ ወንታ እና አቶ አሽትሬ ጢቆ የተባሉ የወረዳው የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ አባላት የታሰሩ ሲሆን፤ በተመሳሳይ በዛላ ወረዳ አምቤ ኃይሌ ቀበሌ ውስጥ፤ የመኢአድ ስብሳቢ አቶ እጅጉ ተክሌን ጨምሮ አስር ሰዎች ከጥር 9 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ ታስረዋል።
እንዲሁም፤ በኦይዳ ወረዳ አምባ ያምባላ ቀበሌ፤ ጥር 6 ቀን ለክልሉ ገዢ ፓርቲ ኢህአዴግ- ደኢህዴግ ማመልከቻ አስገብተው መልቀቂያ የተሰጣቸው የኢህአዴግ አባላት ፤ ጥር 7 ቀን 2004 ዓ.ም በቀጥታ ወደ መኢአድ ጽህፈት ቤት ሄደው አባል ለመሆን እንደሚፈልጉ ማመልከታቸውን የጠቀሱት የህዝብ ግንኙነት ሀላፊዋ፤ ፓርቲያቸው ጥያቄያቸውን ተቀብሎ በበአባልነት እንደመዘገባቸው ከተረጋገጠ በኋላ በማግስቱ መታሰራቸውን ገልፀዋል።
በፓርቲያቸው ሕገ-ደንብ መሠረት ከሌላ ፓርቲ መልቀቂያ የያዘ ሰው፤ ወዲያውኑ የመኢአድ አባል መሆን እንደሚችል፤ ወይዘሪት መሶበወርቅ አስረድተዋል።
በሌላ በኩል በዛላ ወዳ የሌቡላ ቀበሌ ውስጥ፤ የቀበሌው የመኢአድ ሰብሳቢ አቶ ዮሴፍ ያሳ ከጥር 10 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ መታሰራቸውን ያወሱት ሕዝብ ግንኙነት ሀላፊዋ፤ የእስሩ ምክንያት የመሬት ጉዳይ መሆኑንም ገልፀዋል።
በተመሳሳይ በደምባ ጎፋ ወረዳ፤ ጥር 10 ቀን 2004 ዓ.ም አምስት የመኢአድ አባላት መታሰራቸውንም አመልክተዋል።
እኚህኞቹ የታሰሩት ደግሞ፤ “በልማት ለመሳተፍ ፈቃደኛ አልሆናችሁም” እንዲሁም ገበሬውን በዕዳ ለመያዝ በግዳጅ የሚታደለውን ማዳበሪያ አልወሰዳችሁም ተብለው ነው-ወይዘሮ መሶበወርቅ እንዳሉት።
በአንዳንድ ቀበሌዎች ለመታሰር የሚፈለጉ አባወራዎች ሲጠፉ፤ ሚስቶቻቸው የታሰሩበት አጋጣሚ መኖሩንም፤ ወይዘሪት መሶበ ጨምረው ገልፀዋል።
እስካሁን ባላቸው መረጃ መሠረት ከታሰሩት 38 የመኢአድ አባላት በተጨማሪ ፤ሌሎች 21 የፓርቲው አባላትም እንዲታሰሩ ማዘዣ ወጥቶባቸው በታጣቂዎች እየታደኑ እንደሆነም ሀላፊዋ ተናግረዋል።
በደምባ ጎፋ ወረዳ አባ ባንዲ ቀበሌ ውስጥ ደግሞ ዮዳ ሞቶ የተባሉ የመኢአድ አባል ከጥር 8 እስከ ጥር 11 በታሰሩበት ወቅት፤ እርሳቸውን ሊጠይቅ የሄደ ቴዎድሮስ ፌኮ የተባለ ሰው እዛው መታሰሩን፤ ወ/ት መሶበወርቅ አያይዘው ገልፀዋል።
የመኢአድ አባላት ስለታሰሩበት ምክንያት ምላሽ ይሰጡ ዘንድ የየወረዳዎቹን ባለስልጣናት ለማግኘት የተደረገው ጥረት፤ “ስብሰባ ላይ ናቸው” በመባሉ ሊሳካ አልቻለም።
መኢአድ በተለየ መልኩ በደቡብ ክልል በአባላቱ ላይ እየተፈጸመ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዘግናኝ ደረጃ ላይ መድረሱን በማውሳት፤የደኢህዴግ ኢህአዴግ አባላት፦ “የመኢአድ አባል የሆነ ይታሰራል”የሚል ግልጽ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ መሆናቸውን የገለጸው፤ ከሳምንት በፊት ነበር።
እንዲሁም በዳሰነች ምርጫ ክልል ለተወካዮች ም/ቤት ተወዳድረው የነበሩት ወ/ሮ አማረች ገላኔ በ23
ጥይት ተደብድበው እንደተገደሉና የ10 እና 12 ዓመት ህፃናት ልጆቻቸው በጥይት እንደቆሰሉ ፤ ባለቤታቸው አቶ ጌልሄሎ ኩይታ ደግሞ ሀዘናቸውን በመግለፃቸው ብቻ ስለት በያዙ ሰዎች ማስፈራሪያ እንደተፈፀመባቸው መግለፁ ይታወሳል።
“አንዲት ሴት- ያውም የልጆች እናት ፤ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ስለሆነች ብቻ በ 23 ጥይት ተደብድባ ስትገደል እንደቀላል ነገር ነገሩን በዝምታ ማለፋችን ፤አገዛዙ እየፈጸመ ያለውን ግፍ ምን ያህል እየለመድነው እንደመጣንና እንደደነዘዝን የሚያመላክት ነው’ያለው የሆላንዱ ነዋሪ አሸናፊ ክፍሉ፤ “ይህ ዘግናኝ ግድያ በዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ እስኪታወቅ ድረስ፤ ድምፃችንን ልናሰማ ይገባል” ብሏል።