(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ/2011)የኢህአዴግ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በከፍተኛ ስጋትና ውጥረት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አዳራሽ ተጀመረ፡፡
የምክር ቤቱ አባላት ወደ ስብሰባው ሲገቡ ስልክ ይዞ መግባት ከመከልከሉ ሌላ ከፍተኛ ፍተሻ መደረጉ ታውቋል።
ምክር ቤቱ ያለፉትን ወራት የድርጅት ስራዎች አፈጻጸም እንዲሁም በወቅታዊ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ውይይትና ግምገማ በማድረግ አቅጣጫዎች ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በአራቱ የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች መካከል የዓላማና የርዕዮት አንድነት መላላት በመኖሩ እርስ በእርሳቸው እንዲጠራጠሩ አድርጓቸዋል።
በአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ(አዴፓ) እና በኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) መካከል የተሻለ መግባባት ሲኖር ሕወሃት ግን ከሌሎች ብሔራዊ አባል ድርጅቶች ያፈነገጠ አቋም አለው።
ደኢሕዴን የታዛቢነትና የግራ መጋባት አቋም እንደሚታይበት ሲነገር አጋር ድርጅቶች ደግሞ መብታቸው ይበልጥ እንዲከበር በኢህአዴግ ውስጥ ሚና እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ።
አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች ተዋህደው አንድ ፓርቲ ከሆነም አጋር ድርጅቶች የዚሁ ድርጅት አካል እንዲሆኑ ታቅዷል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ዛሬ የተጀመረውን የኢሕአዴግ መደበኛ ስብሰባ መነሻ በማድረግ ሕወሓት “የኢሕአዴግ በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ” መኮላሸቱን መግለጹ ይታወሳል።
ይህም ኢትዮጵያን ለቀውስ እንደዳረጋት ሰሞኑን በተካሄደው የሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ተገልጿል።
ኢትዮጵያን ለመምራት ሃላፊነት የተሸከመው የኢሕአዴግ አመራር ከሚታወቅበትና ከሚለይበት መሰረታዊ እምነቶች ያፈነገጠ፣ የአገሪቱ እውነታ ወደ ጎን በመተው ቅጥ ባጣ ደባል አመለካከት የተበረዘ” ነው ሲል ሕወሃት ግንባሩን ይወቅሳል።እናም የኢሕአዴግ ውህደት አይሳካም ባይ ነው ሕወሃት።
የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ አጋጣሚዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ተደርሷል ያለው የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ በሃገር ደረጃ ኢህአዴግ የጀመረው በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ ሳይሳካ መቅረቱን አትቷል፡፡
ሀገር የሚበትን ተግባር እንዲፈፀም፣ የህዝቦች ስቃይና መከራ እንዲቀጥል አሉታዊ ሚና እየተጫወቱ ያሉ ሃይሎች ዕድል እንዲያገኙ ያደረገው የኢህአዴግ ድክመትና የአመራሩ ክፍተት ነው ሲል ሕወሃት በመግለጫው ጠቅሷል፡፡
የኢህአዴግ መደበኛ ስብሰባ በዚህ የተራራቀ አቋም ውስጥ ሆኖ ከመጀመሩ በፊት አዴፓ እና ኦዴፓ ቀደም ብለው በመወያየት አንድ አቋም መያዛቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
እናም ሕወሃት ሁለቱን ፓርቲዎች ለመለያየት ዘይዶ የገባው አጀንዳ ሊሳካ እንደማይችል አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ አባል ለኢሳት ገልጸዋል።