የዊክሊክሱ መስራች ጁሊያን አሳንጅ በቁጥጥር ስር ዋለ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 3/2011)በለንደን የኢኳዶር ኤምባሲ ለሰባት ዓመታት ተጠልሎ የነበረው የዊክሊክሱ መስራች ጁሊያን አሳንጅ በቁጥጥር ስር ዋለ።

በምዕራባውያን መንግስታት በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው አሳንጅ ለኢኳዶር መንግስት ያቀረበው የፖለቲካ ጥገኝነት ጥያቄ ውድቅ መሆኑን ተከትሎ በእንግሊዝ ፖሊስ እጅ መውደቁን ቢቢሲ ዘግቧል።

አሜሪካን አሳንጅ ተላልፎ እንዲሰጣት መጠየቋ የሚታወስ ነው። ጉዳዩን የለንደኑ ዌስት ሚኒስትር ፍርድ ቤት መመልከት መጀመሩ ታውቋል።

የኢኳዶር መንግስት በስዊዲን ክስ የቀረበበትን ጁሊያን አሳንጅን ለሰባት አመት ከጠለለበት የለንደን ኤምባሲ እንዲወጣ ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ የእንግሊዝ ፖሊሶች በካቴና እጆቹን አስረው እንዳሰውጡትና ወደለንደን ወህኒ ቤት መውሰዳቸው ታውቋል።

በወሲብ ጥቃት ክስ የመሰረተው የሲውዲን አቃቤ ህግ ክሱን ቢያነሳም አሜሪካ ተላልፎ እንዲሰጣት ግፊት ስታደርግ ቆይታለች።

የእንግሊዝ ፖሊስ እንዳስታውቀው በአሜሪካ ስም በለንደን እንዲታሰር የተደረገው የዊክሊክስ መስራች ጁሊያን አሳንጅ በዌስት ሚኒስትር ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ታውቋል።

በእንግሊዝ የኤኳዶር አምባሳደር የአሳንጅ የፖለቲካ ጥገኝነት ጥያቄ ተቀባይነት እንዳላገኘና የእንግሊዝ ፖሊስ በኤምባሲው ገብቶ አሳንጅን መውሰድ እንደሚችል ከገለጹ በኋላ እስሩ መፈጸሙን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኤኳዶር ፕሬዝዳንት ሌኒን ሞሬኖ በቲውተር ገጻቸው ላይ አሳንጅ በኤምባሲው ቆይታው ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች በተደጋጋሚ ሲጥስ እንደነበረ በመጥቀስ የፖለቲካ ጥገኝነት ጥያቄው እንዳልተፈቀደ ገልጸዋል።

ዊሊያም አሳንጅ የእንግሊዝ ፍርድ ቤት ቀርቦ ለአሜሪካ ተላልፎ ይሰጥ አይሰጥ የሚል ውሳኔ ይጠብቀዋል ተብሏል።

አሜሪካ ከባድ ሚስጥሮችን በማውጣት የሃገር ደህንነትን ስጋት ውስጥ ከቶታል በሚል ዊሊያም አሳንጅ በጥብቅ ስትፈልገው እንደነበር ዘገባዎች ያመለክታሉ።