የኢህአዴግ መንግሥት ከተቃዋሚዎች ጋር የሚደረግ የክርክር መድረክ እንዳዘጋጀ እየተናገረ ነው

የካቲት 12 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-‹‹የ ኢህአዴግ መንግሥት ከተቃዋሚዎች ጋር የሚደረግ የክርክር መድረክ እንዳዘጋጀ እየተናገረ ያለው ፤ በአገሪቱ በቂ የፖለቲካ መንቀሳቀሻ ሜዳ አለ በማለት ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማታለል ነው”ሲል በቅርቡ ከፖለቲካ ፓርቶዎች የምክክር መድረክ ራሱን ያገለለው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ገለጸ።

የመኢአድ ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ታሪኩ  መኢአድ፤ የፓርቲዎችን የጋራ የምክክር መድረክ ተቀላቅሎ የምርጫ ሥነ ምግባር ደንቡን የፈረመው ‘በፓርቲው አባላት ላይ የሚፈጽመው ግድያና እስራት ይቆማል፣ የ2002ቱ ምርጫ ፍትሐዊ እንዲሆን ዋስትና ይሰጣል’ የሚል እምነት ይዞ የነበረ ቢሆንም፤ ይህ ተስፋው እውን ሊሆንለት እንዳልቻለ አመልክተዋል።

ስምምነቱ በተፈረመ ማግስት የኢሕአዴግ ካድሬዎች በየገጠሩ እየተዘዋወሩ ‹‹ኃይሉ ሻውል ለእኛ እጃቸውን ሰጥተዋል›› በማለት የስም ማጥፋት ዘመቻ መጀመራቸውን የሚናገሩት አቶ ተስፋዬ፣ ፓርቲዎች የተፈራረሙት ቀለም ሳይደርቅ የመኢአድ አባላት ላይ የሚፈጽመው እስርና ግድያ ተጠናክሮ መቀጠሉንና ‘አንድ ለአምስት’ በሚል የአፈና መዋቅር በመመሥረትም ገዥው ፓርቲ በጡንቻ ሥልጣን መያዙን ይናገራሉ፡፡

በመሆኑም፤ በምርጫ ዙሪያ  ፓርቲያቸው ከኢሕአዴግ ጋር መሥራቱ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን ሆኖ ስላገኘው፤ ራሱን ከፓርቲዎች የጋራ የምክክር መድረክ አባልነቱ አግልሏል-ዋና ፀሀፊው እንዳሉት።

 ‹‹አማራጩ የኢሕአዴግ አጃቢ መሆን ሳይሆን ሰፊ የፖለቲካ ሥራ በመሥራት ሕዝቡን ከዳር እስከ ዳር ማነሳሳት ነው፤›› ሲሉም አክለዋል።

‹‹መንግሥት ውይይቱን ያዘጋጀው በአገሪቱ በቂ የፖለቲካ መንቀሳቀሻ ሜዳ አለ በማለት ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማታለል ነው፤›› የሚሉት አቶ ተስፋዬ፣ ኢሕአዴግ ትክክለኛ የፖለቲካ ውይይት እንዲካሄድ ከፈለገ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ጠንካራ ፓርቲዎች በውይይቱ የሚሳተፉበትን ዕድል ሊያመቻች ይገባው እንደነበር ያስረዳሉ፡፡

መንግስት በቅርቡ ለፓርቲዎች ድጎማ በሚል ወጪ ካደረገው 10 ሚሊዮን ብር ውስጥ፤የምክክር መድረክ አባላት የሆኑት የ ኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ(ኢዴፓ) እና የ ኢትዮጵያውያን ራዕይ ፓርቲ የ አንበሳውን ድርሻ ሲያገኙ ሌሎች ፓርቲዎች ያገኙት ገንዘብ ግን በጣም አነስተኛ ነው።

ኢዴፓ 300 ሺህ ብር፣የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ 180 ሺህ ብር ሲያገኙ መኢአድ 3 ሺ 500 ብር ብቻ ማግኘቱን የጠቆሙት ዋና ፀሀፊው፤” ኢዴፓና ኢራፓ ብቻ በምን መለኪያ ነው ከሌሎቹ በተለየ ሁኔታ ይህን ያህል ድጋፍ ያገኙት?” በማለት ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ አቅርበው፦”ገዥው ፓርቲ ከራሱ ድርሻ ቀንሶ ለፈለገው ፓርቲ መስጠት ይችላል”የሚል መልስ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

“ይህ ክስተትም ኢሕአዴግና የምክክር መድረኩ አባላት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ መሆናቸውን ቁልጭ አድርጐ የሚያሳይ ነው”ይላሉ አቶ ተስፋዬ።

 በቅርቡ አቶ መለስ ዜናዊ በፓርላማ ሪፖርት ሲያቀርቡ፤ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ፤የምርጫ ሥነ ምግባር ደንቡ የአገሪቱ ሕግ ሆኖ ቢወጣም፣ መንግሥት የምርጫ ሕጉን መቀበል አለባችሁ የሚል ቅድመ ሁኔታ እያስቀመጠ ድርጅታቸው ለሚያቀርበው የእንደራደር ጥያቄ ትርጉሙ ግልጽ ያልሆነ የማንበርከክ ስትራቴጂ እየተከተለ እንደሚገኝ  መግለፃቸው ይታወሳል።

ወጪ ከተደረገው 10 ሚሊዮን ብር ላይ  3 ሺ 500 ብር ብቻ የደረሰው መኢአድ ያንኑ ገንዘብም በምን ላይ እንዳዋለው ኦዲት አስደርጐ እንዲያቀርብ በምርጫ ቦርድ መጠየቁን የገለፁት አቶ ተስፋዬ፤ ፓርቲያቸው፣ ለ3 ሺ 500 ብር ወጪ፤ በአሥራ አምስት ሺሕና በሃያ ሺሕ ብር ክፍያ ኦዲተር ቀጥሮ ማሠራቱ አግባብ ሆኖ ስላላገኘው፣ ከምርጫ ቦርድ የተቀበለውን ገንዘብ እንዳለ ለመመለስ መገደዱን አመልክተዋል።
ኢህአዴግ ከመሰሎቹና ከራሱ አጋር ድርጅቶች ጋር ሊያደርገው የወሰነው ውይይት፤ፈፅሞ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር እንደሚደረግ ተደርጎ ሊታይ እንደማይገባ ያስረዱት ዋና ፀሀፊው፤ ‹‹ገዥው ፓርቲ አንዱን በጠላትነት ሌላውን በወዳጅነት የሚፈርጅበትን አሠራርና በግብር ከፋዩ ሕዝብ የሚተዳደረውን ሚዲያ በሞኖፖል መቆጣጠሩን በማቆም ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚወያዩበትን ሁኔታ እንዲያመቻች አስገንዝበዋል።
_____________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide