(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 29/2011)የአፋር ህዝብ ፓርቲ በአፋር ክልል በሁለት ከተሞች ጽሕፈት ቤት በመክፈት በሃገር ቤት በይፋ መንቀሳቀስ ጀመረ።
የመጀመሪውያውንም ጉባዔ ማካሄዱን አስታወቋል።
ፓርቲው ከምርጫ ቦርድ የመንቀሳቀሻ ፍቃድ እንደተሰጠውም ታውቋል።
በህጋዊ መንገድ ተመዝግቦ የፓርቲ እውቅና እስኪያገኝ በጊዜያዊነት በተሰጠው ፍቃድ በአፋር ክልል በተለያዩ ወረዳዎች ተጨማሪ ጽሕፈት ቤቶችን ለመክፈት በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቋል።
ባለፈው ቅዳሜ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቹ በተገኙበት የጽህፈት ቤት ምረቃት ያደረገው የአፋር ህዝብ ፓርቲ በክልሉ ሁለንተናዊ ገጽታዎች ላይ አወንታዊ አስተዋጽኦ ለማድረግ መዘጋጀቱን ገልጿል።
የተመሰረተው እንደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2006 ነው።
ውልደቱን በውጭ ሃገር አድርጎ በተለያዩ የትግል አማራጮች በመጠቀም የአፋር ህዝብን ከጭቆና ለማላቀቅ በሚል የተመሰረተው የአፋር ህዝብ ፓርቲ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት፣ ከኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር ኦዴግና ከሲዳማ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄን የመሰረተ ፓርቲ ነው።
በሀገር ውስጥ በህቡዕ በመንቀሳቀስ ላለፉት 10 ዓመታት ህዝቡን በነበረው ግዜ መንግስት ላይ እንዲያመጽና ለለውጥ እንዲነሳ ውስጣዊ ትግሎችን ሲያካሂድ እንደነበር ከፓርቲው አካባቢ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአፋር ህዝብ ፓርቲ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ለውጥ ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት ለመግባት ከውሰኑ ድርጅቶች አንዱ ነበር።
የፓርቲው አመራሮች ወደ ሀገር ቤት በማቅናት በሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ ለመጀመር ቢዘጋጁም የአፋር ክልልን የሚያስተዳድሩት አመራሮች የለውጡ እንቅፋት በመሆናቸው ወደ ክልል መድረስ እንዳልቻሉ ነው የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር ኮንቴ ሙሳ የሚገልጹት።
የአፋር ህዝብ በለውጥ ንቅናቄ ውስጥ ባለበት ወቅት ወደ አፋር ለማምራት የተዘጋጁት የአፋር ህዝብ ፓርቲ አመራሮች ከክልሉ ገዢ ፓርቲ ሰዎች በገጠማቸው ፈተና ከአዲስ አበባ ሳይንቀሳቀሱ ለአንድ ወር ቆይተው ከሀገር ለመውጣት ተገደዋል።
ይሁንና የአፋር ህዝብ ትግል ተፋፍሞ የአቶ ስዩም አወል አመራር ሲፈራርስና አዲስ መሪ ለክልሉ ሲሰየም ነገሮች መስመር መያዝ መጀመራቸውን ነው ዶክተር ኮንቴ የሚያስረዱት።
ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሃገር ቤት በመግባት እንቅስቃሴ የጀመረው የአፋር ህዝብ ፓርቲ በሁለት የአፋር ከተሞች ጽሕፈት ቤት መክፈት ችሏል።
ባለፈው ቅዳሜ በዱብቲና ሰመራ ከተሞች ጽሕፈት ቤቱን የከፈተው ፓርቲው በይፋ ወደ እንቅስቃሴ መግባቱንም አስታውቋል።
የፓርቲውን እንቅስቃሴ በህቡዕ ከሀገር ቤት ሲመሩ የነበሩ አባላቶቹና ሌሎች ደጋፊዎቹ በተገኙበት የጽሕፈት ቤት ምረቃ ስነስርዓት ያከናወነው የአፋር ህዝብ ፓርቲ ከምርጫ ቦርድ የመንቀሳቀሻ ፍቃድ ማግኘቱን ገልጿል።
ፓርቲው በሌሎች የአፋር ክልል ወረዳዎችም ጽሕፈት ቤት ለመክፈት በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቋል።