(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 25/2011)የእንግሊዝ ሙዚየም የአጼ ቴዎድሮስን ፀጉር ለኢትዮጵያ ለመመለስ መስማማቱ ተገለጸ።
ሙዚየሙ የአጼ ቴዎድሮስን ፀጉር ለመመለስ ያሰበው በኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ ነው ተብሏል።
የአጼ ቴዎድሮስ ጸጉር ባለፈው ዓመት በሙዚየሙ ውስጥ እና በድረገጽ ለዕይታ በመብቃቱ ብዙዎችን ኢትዮጵያውያን አስቆጥቶ እንደነበር ይነገራል።
አጼ ቴዎድሮስ ከ150 ዓመታት በፊት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1968 መቅደላ ላይ ለእንግሊዝ ወታደሮች እጅ አልሰጥም ብለው በጀግንነት መንፈስ ራሳቸውን መግደላቸው አይዘነጋም።
ይህንን ተከትሎ ታዲያ ወታደሮቹ የአጼ ቴዎድሮስን ፀጉር ጨምሮ በርካታ ነዋየ ቅድሳትን እንዲሁም የብራና መጽሐፍትን ዘርፈው መውሰዳቸው ይታወቃል።
በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በጉዳዩ ዙሪያ ለመወያየት ለሐሙስ ቀጠሮ መያዙን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ኤምባሲ የብሪታንያ ሙዚየም እዚህ ውሳኔ ላይ በመድረሱ ምስጋና አቅርቧል።
ይሕ በመሆኑም የልዑል አለማየሁን አጽም ጨምሮ መጽሐፍትና ሌሎች ንዋያ ቅድሳት ወደ ሀገራቸው ሊመለሱ ይችላሉ የሚል ተስፋን አጭሯል።
የአጼ ቴዎድሮስ ጸጉር በህልፈታቸው ወቅት መቅደላ ላይ ምስላቸውን ካስቀረው ሰዓሊ ቤተዘመዶች ቤት የነበረ ሲሆን፥ እአአ በ1959 ለሙዚየሙ ማስረከባቸው ይነገራል።
በቅኝ ግዛትና ከዚያም በኋላ የተዘረፉ 90 በመቶ የሚደርሱ የአፍሪካውያን የጥበብ ስራዎች ከአህጉሪቱ ውጪ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።