የአጫሉ ሁንዴሳ የሙዚቃ ኮንሰርት ተሰረዘ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 26/2010)

ታዋቂው የኦሮምኛ ሙዚቃ አቀንቃኝ አጫሉ ሁንዴሳ በጊዮን ሆቴል ያዘጋጀው የሙዚቃ ኮንሰርት ተሰረዘ።

የአዲስ አበባ አስተዳደር ለጉዳዩ በሰጠው ምላሽ የሙዚቃ ኮንሰርቱ የተሰረዘው በጸጥታ ችግር ምክንያት መሆኑን አመልክቷል።

ታዋቂው ድምጻዊ አጫሉ ሁንዴሳ በግዮን ሆቴል ሊያካሂድ የነበረው የሙዚቃ ኮንሰርት መሰረዝ በርካታ ኢትዮጵያንን ያስቆጣ ሆኗል።

የመንግስታትን ርምጃ በመቃወም በማህበራዊ ድረገጾች ከፍተኛ ትችቶች እየቀረቡ መሆናቸው ታውቋል።

በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ በሆኑ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ላይ የሚደርሰው ጫና እንዲቆምም ጥሪ ቀርቧል።

የሙዚቃ ኮንሰርቱን ለማካሄድ መርሃ ግብር የተያዘው ለህዳር 13/2010 እንደነበርም ተገልጿል።

የአዲስ አበባ መስተዳድር ለኮንሰርቱ ፍቃድ በመስጠቱ ፕሮግራሙን ለማካሄድ ዝግጅት በተጠናቀቀበት ወቅት የስረዛው ደብዳቤ መከተሉም ተመልክቷል።

ጥቅምት 13/2010 ድምጻዊው አጫሉ ሁንዴሳ የሙዚቃ ኮንሰርት በአዲስ አበባ ጊዮን ሆቴል እንዲካሄድ ፍቃድ የሰጠው የአዲስ አበባ መስተዳድር ከ10 ቀናት በኋላ በጻፈው ሌላ ደብዳቤ ፍቃዱ መሰረዙን አስታውቋል።

የሰጠው ምክንያት ደግሞ የጸጥታ ችግር የሚል እንደሆነም ከደብዳቤው መረዳት ተችሏል።

ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ በተደጋጋሚ የሙዚቃ ኮንሰርቱ በመንግስት የሚሰረዝበት አርቲስት መሆኑ ይታወሳል።

ድምጻዊ አጫሉ ሁንዴሳም በተመሳሳይ በሀገሩ ምድር የሙዚቃ ኮንሰርቱን እንዳያቀርብ የተከለከለ ሙዚቀኛ ሆኖ ተመዝግቧል።