በዶክተር መረራ ጉዲና ላይ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ተሰጠ 

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 26/2010)

የፌደራሉ አቃቢ ህግ በዶክተር መረራ ጉዲና ላይ ተጨማሪ ምስክሮችን ማቅረብ ባለመቻሉና በቀረቡት ማስረጃዎች ውሳኔ እንዲሰጠው በመጠየቁ ችሎቱ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሰጠ።

በዶክተር መረራ ጉዲና ላይ የቀረቡት ምስክሮች ከቤታቸው ጽሁፎች ሲወሰዱ ማየታቸውን ከመግለጽ ውጪ ስለጽሁፎቹ ይዘትም ሆነ በሌላ ጉዳይ ላይ የሰጡት ምስክርነት አለመኖሩ ተገልጿል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ዶክተር መረራ ጉዲና በብይን በነጻ የመፈታታቸው ጉዳይ የሰፋ መሆኑን አንድ የህግ ባለሙያ ለኢሳት ገልጸዋል።

የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ይዞታ ላይ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ተገኝተው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሰዋል በሚል የታሰሩት ዶክተር መረራ ጉዲና የሽብር ክስ እንደተመሰረተባቸው ይታወሳል።

በሂደትም ክሱ ተሻሽሎ ከአሸባሪነት ሕገመንግስታዊውን ስርአት በሃይል የመናድ ሙከራ በሚል ክሱ ከተሻሻለ በኋላ አቃቢ ህግ ምስክሮችን ማቅረብ ጀምሮ ነበር።

ባለፈው አርብ ህዳር 22/2010 የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ተጨማሪ የአቃቢ ህግ ምስክሮች ሊሰሙ በተቀጠረበት ወቅት ተጨማሪዎቹ ምስክሮች ባለመገኘታቸውና አቃቢ ህግም እንደማይፈልጋቸው በመግለጹ ችሎቱ ለብይን ቀጠሮ ሰጥቷል።

አቃቢ ህግ በቀረቡት ማስረጃዎች መሰረትም ዶክተር መረራ ይከራከሩ ዘንድ ፍርድ ቤቱ ብይን እንዲሰጥለት መጠየቁም ተመልክቷል።

በአቃቢ ህግ በኩል ቤት ሲበረበር አየን ከማለት ውጪ ከቤቱ ውስጥና ከኮምፒዩተር ስለተገኙት ሰነዶች ምንነት በማያውቁ ምስክሮች ቃል እንዲሁም በፖለቲካ ፕሮግራም ሰነዶችና የግል ኢሜል ልውውጥ ወዘተ ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ብይን የሚሰጥበት ሕጋዊ መሰረት አለመኖሩን የህግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የህግ ባለሙያዎቹ እንደሚሉት ፍርድ ቤቶች የፖለቲካ ውሳኔ የሚተላለፍባቸው በመሆኑ የሚሆነውን ለመተንበይ ህጋዊውን ሁኔታ መተንተን ብቻውን በቂ አይደለም።

ፍርድ ቤቱ በዶክተር መረራ ላይ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ የሰጠው ለታህሳስ 25/2010 መሆኑ ታውቋል።

በዕለቱ ዶክተር መረራ በነጻ ሊለቀቁ ወይንም የመከላከያ ማስረጃዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ሊጠየቁ እንደሚችሉ ህጋዊውን ስርአት መሰረት በማድረግ የህግ ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ።