የአዲስ አበባ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ማዕከላት በከፍተኛ ሙስና ተዘፍቀዋል

ግንቦት ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአዲስ አበባ የሚገኙ 32 የቴክኒክና ሙያ የትምህርት ተቋማት ከግዥና ንብረት አስተዳደር ጋር በተያያዘ በከፍተኛ ሙስናና ብልሹ አሠራር ውስጥ ተዘፍቀው እንደሚገኙ አንድ ጥናት አረጋገጠ፡፡

የፌዴራል የሥነምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሸን በተቋማቱ ላይ ያካሄደውን ጥናት በዛሬው ዕለት ይፋ ባደረገበት ወቅት የሰለጠነ የሰው ኃይል በብቃት የማፍራት ኃላፊነት የተጣለባቸው እነዚሁ ተቋማት ለመማር ማስተማር ሒደቱ ወሳኝ የሆኑ ግዥዎችን ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ እንደማያካሂዱ አጋልጧል፡፡

አገሪቱ ካላት ትንሸና ውስን ሀብት አንጻር በየዓመቱ ከፍተኛ በጀት የሚበጀትላቸው እነዚሁ  የትምህርት ተቋማት በተለይ ከግዥ ጋር ተያይዞ አስከፊ በሚባል ደረጃ ችግር እንዳለባቸው ጥናቱ አሳይቷል፡፡ከታዩት ሙስናና ብልሹ አሠራሮች መካከል ግዥን በዕቅድና ፕሮግራም አለመምራት፣ለሚገዙ  ዕቃዎች

የቴክኒክ ፍላጎት መግለጫ( ሰፔስፊኬሸን) አለማዘጋጀት፣ግልጽነት ያለው የጨረታ አከፋፈትና  ሒደትን አለመከተል፣አንድ አቅራቢን በተለየ ሁኔታ ሊጋብዝ በሚችል ሁኔታ የእቃዎችን መለያ  ( ብራንድ) በመግለጽ ግዥ መፈጸም፣በተደጋጋሚ ከአንድ አቅራቢ ብቻ ግዥ መፈጸም እና የመሳሰሉት ተጠቅሰዋል፡፡

አብዛኛዎቹ የስልጠና ተቋማት ውስጥ የሚከናወኑ ግዥዎች ከትምህርት ክፍሎች ጋር በተጠናከረ ሁኔታ ያልተቀናጁና የግዥ ዕቅድና መርሃግብር

የሌላቸው መሆኑን ጥናቱ ያብራራል፡፡የግዥ ሥርዓቱ ለሙስና በመጋለጡ ሰልጣኞች በወቅቱ ሊያገኙ የሚገባቸውን ሥልጠናዎች እንዳያገኙ በማድረግ የክህሎት ክፍተት ኖሯቸው እንዲመረቁ ምክንያት መሆኑን፣ ይህ ደግሞ ትውልድን

የሚጎዳ የከፋ አድራጎት መሆኑ ተመልክቷል፡፡

 

የንብረት አስተዳደርንም በተመለከተ የአዲስአበባ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ማዕከላት እንደ ግዥው ሁሉ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳሉ ጥናቱ አሳይቷል፡፡ታይተዋል ከተባሉት ችግሮች መካከል ንብረቶችን ሲገዙ ጠንካራና

ወጥነት ያለው የቁጥጥር ሥርዓት የሌላቸው መሆኑ፣ንብረቶች ለስርቆት በሚያመች  መልኩ ተጋልጠው መያዛቸው፣የተደራጀ የቋሚ ንብረቶች የምዝገባና ቁጥጥር ሥርዓት አለመኖር፣ንብረቶችን ያለሥራ አከማችቶ መያዝ፣የእቃ ገቢና ወጪ ሰነዶችን በአግባቡ ሥራ ላይ  አለማዋልና የመሳሰሉት ችግሮች ለሙስናና ለብልሹ አሠራር የሚያጋልጡ መሆናቸውን የኮሚሸኑ ጥናት ያረጋግጣል፡፡

በአዲሰ አበባ 32 ያህል የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማት የሚገኙ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ስድሰቱ ኮሌጆች ሲሆኑ የተቀሩተረ የሥልጠና ተቋማት ናቸው፡፡ለእነዚህ ተቋማት በጠቅላላው በ2004 በጀት ዓመት 180ሺ900 ሚሊየን ብር በጀት ተመድቦላቸዋል፡፡

አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከአገሪቱ ዓመታዊ በጀት ውስጥ ግዥ ከ60-70 በመቶ ድርሻ ሲኖረው ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት(ጂ.ዲ.ፒ) ደግሞ እስከ 15 በመቶ ድርሻ እንዳለው ታውቋል፡:

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide