አንድነት ፓርቲ መንግስት ያወጣውን የቅድመ ምርመራ ህግ እንዲያነሳ ጠየቀ

ግንቦት ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ፓርቲው ዛሬ ” ከመቃብር ተመልሶ የመጣውን የሳንሱር መቀስ እንቃወመዋለን ወደ መቃብሩ እንዲመለስም እንታገለዋለን ” በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ ፣ ብርሀንና ሰላም ራሱን ከተጠያቂነት ለማዳን በማስመሰል ካዘጋጀው ውል ጀርባ ሌላ እጅ እንዳለ ይጠረጠራል በማለት ከገለጠ በሁዋላ፣ አዋጁ የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ ተብሎ በሚታሰበው ህገ መንግስት አንቀጽ 29 ላይ የቅድመ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ ነው የሚለውን ግንጋጌ በአደባባይ የሚጥስ ነው ሰል አትቷል።

ከዚህ በፊት ህገመንግስት ተጣሰብኝ፣ ተናደብኝ የሚለው ገዢ ፓርቲ ዝምታ ከብርሀንና ሰላም የሳንሱር ህግ ጥሰት ጀርባ የቆመው አካል ማን እንደሆነ የሚያመለክት ነው የሚለው አንድነት፣ ለዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ፣ ለነቃ ትውለድ ቀረጻ፣ ለልማትና እድገት አስፈላጊ ነው በሚባለው የነጻ ፕሬስ ላይ ከዚህ በፊት የተከፈተበት የተቀነባበረ የመቆጣጠር እና የማጥፋት ዘመቻ አልበቃ ብሎ ጭራሽ ለታላቛ ኢትዮጵያ የሚመጥን ነጻ ፕሬስ በሌለበትና ሃላፊነት የሚሰማው መንግስት ካለ ድጋፍ መቸር በሚገባበት ወቅት በሀገራችን እየተደረገ ያለው ግን ያሉትን አንድና ሁለት ነጻ ጋዜጦች ማጥፋት ላይ ያነጣጠረ ነው ብሎአል።

አንድነት በመግለጫው ” የኢህአዴግ መንግስት በሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎች እና በልማታዊ ጋዜጠኞች አማካኝነት በለውጥ እና በእድገት ጎዳና እየዘለቅዩ ነው እያለ ዘወትር የሚናገረው ገዢው ፓርቲ ለውጡና እድገቱ ካለ ለምን ይርበናል፣ ለምን በቤት እጦት እንከራተታለን፣ ሀሳባችንን በነጻነት ለመግለጽ ለምን አንችልም ፣ መስዋትነት ተከፍሎበታል የምትሉት ዲሞክራሲ የት አለ ከሚለው የህዝብ ይፋዊ ጥያቄ ጋር እየተንገራገጨ ይገኛል ብሎአል። ለጥቂት ነጻ ጋዜጦች ማፈኛ ሲባል ከተዘጋጁት የፕሬስ ህግ፣ ጸረ ሽብረተንነት ህግና እንደ አዲስ ዘመን አይነት የመንግስት ሚዲያዎች ላይ ከሚሰነዘሩ ማስፈራሪያዎች በተጨማሪም በማተሚያ ቤት በኩል የሳንሱር ህግ በማበጀት ለማጥፋት የተያዘው መንገድ አጥፊ ነው የሚለው አንድነት ፣ አፈሩን አራግፎ ከመቃብር የተነሳውን የሳንሱር መቀስ ኢትዮጵያ ህዝብ በመቃወም በሞት አፋፍ ላይ ያለውን ፕሬስ እንዲታደገው እንጠይቃለን ሲል ደምድማል።

ብርሀንና ሰላም እና ቦሌ ማተሚያ ቤቶች በጋዜጦች ላይ ቅድመ ምርመራ የሚፈቅድ ውል አሳታሚዎች እንዲፈርሙ እያስገደዱ እንደሚገኙ መዘገባችን ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide