ኢህአዴግ መጅሊስ እንዲፈርስ ቢወሰንም ሙስሊሞቹ ግን ትግሉ ይቀጥላል ይላሉ

ግንቦት ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ኢህአዴግ መንግሥት በሙስሊሙ ማህበረሰብ በተፈጠረበት ጫና ሃይማኖቱን በበላይነት ሲመራ የነበረውንና በመንግሥት የሚደገፈውን መጅሊስ እንዲፈርስ ባለፈው ሃሙስ ውሳኔ ማሳለፉን ምንጮች አስታወቁ፡፡

ዛሬ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በመጅሊስ የተጠሩ የአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ሙስሊም ማህበረሰቦች ከፌዴራል ጉዳዮች ጽ/ቤት ተወካዮች ጋር የተወያዩ ሲሆን ከሰኔ መጀመሪያ እስከ ሐምሌ 2004 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ አዲስ መጅሊስ በምርጫ ይቋቋማል በሚል በመንግሥት ቃል ተገብቷል። ይሁን እንጅ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄ አለመመለሱን የሙስሊሙ ማህበረሰብ ጊዜያዊ ኮሚቴ አባላት ለማህበረሰቡ ገልጸዋል፡፡

በውይይታቸው ላይ የሙስሊሙ ማህበረሰብ እራሱ ባቋቋመው ነፃ፣ ገለልተኛና ታማኝ የኮሚቴ አባላት መጪው ምርጫው በመስጂድ እንዲካሄድ ቢጠይቅም በመንግሥት በኩል አልተፈቀደም ያሉን ምንጫችን ፣ የኢህአዴግ መንግሥት የተስማማው በካድሬነት ያስቀመጣቸው የዑላማ ምክር ቤት ምርጫውን በበላይነት እንዲያካሄዱና ፈረሰ የተባለው መጅሊስ ከፌዴራል ጉዳዮች ጋር በመተባበር በላያችን ላይ የጫነውን የአሕባሽ አስተምህሮ  ሊያስቀጥል የሚችል የይስሙላ መጅሊስ በቀበሌ ሊያቋቁም ነው ሲሉ አክለዋል።

የሙስሊሙ ማህበረሰብ ተወካዮች በመጪው ዓርብ የጁምዓ ፀሎት ላይ ለሕዝበ ሙስሊሙ ሁኔታውን በማስረዳት በቀጣይ የትግል አካሄዳቸው ላይ ለመነጋገር ሃሳብ እንዳለ አንድ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የሃይማኖት አባት ለዘጋቢያችን አስታውቀዋል፡፡

ይሁን እንጅ ለሕዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች መፍትሄ ለማፈላለግ የተቋቋመው ኮሚቴ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ፡   ” የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ያልተመረጠ አመራርም ሲሰጠው የቆየውን መተዳደሪያ ደንቡን መርምሮ ራሱን ከሀላፊነት ለማግለል በመወሰኑ ህዝበ ሙስሊሙ ያነሳው ጥያቄ ምላሽ የማግኘት ሂደት ላይ መሆኑን እንገነዘባለን ብሎአል።

የስልጣን ሽግግሩ ህዝባዊነት በሌላውና የመጅሊሱ መዋቅር አካልና አጋር ለሆነው እንዲሁም መዋቅራዊ አቅም ለሌለው የኡላማዎች ምክር ቤት መሰጠቱ አግባብ እንዳልሆነም ይሰማናል ካለ በሁዋላ፣  ህዝበ ሙስሊሙ በቅርቡ ለሚደረገው የመጅሊስ ምርጫ ይሆኑኛል የሚላቸውን ተወካዮች ለመምረጥ ብርቱ ዝግጅት ከማድረግ በተጨማሪ ከኮሚቴው ጎን በመሆን አፈጻጻሙ ነጻ፣ ሰላማዊ፣ ግልጽና ፍትሀዊ መሆኑን በንቃት እንዲከታተል ጥሪ እናደርጋለን ብሎአል።  በመላ አገሪቱ ያለው ህዝባዊ ጥያቄ ተመሳሳይ በመሆኑ መንግስት ካነሳው ጥያቄ ጋር በተያያዘ ምክንያት ለእስር የተዳረጉ እንዲፈቱ ፣ ማስፈራራቶችና የሀይል እርምጃዎች እንዲቆሙ ያደርግ ዘንድ አቤቱታችንን እናቀርባለን… ወደ ብጥብጥ ሊያስገቡ የሚችሉ ድርጊቶች በመስጊዶችም ሆነ በማንኛውም ቦታ እንዳይከሰቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ በአላህ ስም እንጤኢቃለን።” በማለት ግልጧል::

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide