የአዲስ አበባ ከንቲባ የከተማዋን የጸጥታ ጉዳይ ለኦሮምያ ምክር ቤትም ሪፖርት እንዲያቀርቡ ታዘዙ

መጋቢት ፫(ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአዲስ አበባንና የኦሮምያን የጸጥታ ሁኔታ ለማስተሳሰር፣ የኦሮምያን ልዩ ሃይልና የፌደራል ፖሊሶችን በጋራ በአዲስ አበባ ለመጠቀም ሲባል፣ መስተዳድሩ የጸጥታ ጉዳዮችን ለጨፌ ኦሮምያም ጭምር ሪፖርት እንዲያደርግ ታዟል።

የእቅዱ ዋና ነዳፊ የሆኑት የጠ/ሚኒስትሩ አማካሪ አባይ ጸሃየ፣ ጸጥታን በተመለከተ የኦሮምያ ምክር ቤት ሪፖርት እንዲቀርብለት፣ የልማት ጉዳዮችን በተለይ መሬትን በተመለከተ ደግሞ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ሪፖርት እንዲቀርብለት አዘዋል። ምርጫው ተጠናቆ አዲስ ምክር ቤት እስከሚመሰረት ድረስ በዚህ መንገድ እንዲቀጥል  አባይ ጸሃየ ቢያዝዙም፣ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ሳይቀበሉት ቀርተዋል። ትእዛዙ ወደ ምክትል ከንቲባው አባተ ስጦታው እንዲወርድ ቢደረገም፣ አቶ አባተ ኦሮምኛ አይችሉም በሚል አቶ ድሪባ በግድ እንዲቀበሉት ተደርጓል።

ከንቲባ ድሪባ ጨፌ ኦሮምያ ተገኝተው ሪፖርት የቃረቡ ቢሆንም፣ ከምክር ቤት አባላት የተነሱትን ጥያቄዎች መመለስ ሳይችሉ ቀርተዋል። ከንቲባ ድሪባ ” የአዲስ አበባ የጸጥታ ጉዳይ ለምርጫው ሲባል በኦሮምያ ምክር ቤት እንዲደመጥ ተወስኗል” ብለዋል።

በአዲሱ አሰራር የኦሮምያ ክልል ምን እንደሚያገኙ የጠየቁት የምክር ቤት አባላት በቂ ምላሽ አላገኙም። ይሁን እንጅ አሁንም መሬት ለማስፋት፣ የኦሮምያና የአዲስ አበባ ክልሎችን በማጣረስና ውሳኔዎችን በመደራራብ ችግር ለመፍጠር ታስቦ የተካሄ እንዳይሆን ፣ አካሄዱም ኢህአዴግን ለከፋ ችግር ሊዳርገው እንደሚችል ተናግረዋል።