ሐምሌ ፲፫ ( አሥራ ሦስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአምቦ፣ ነቀምቴ፣ ወሊሶ፣ ግንጪ፣ ሻሸመኔ፣ባሌ፣ መንዲ ፣ ነጆ፣ ሆለታና ሌሎችም በርካታ ከተሞች ላለፉት 3 ቀናት ሲካሄድ የነበረው የነጋዴዎች ተቃውሞ፣ ዛሬ ሃሙስ ወደ አዲስ አበባ በመሸጋገር፣ በተለያዩ የመዲናዋ ክፍሎች የሚገኙ አነስተኛ ነጋዴዎች የንግድ ድርጅቶቻቸውን በመዝጋት ተቃውሞአቸውን እየገለጹ ነው። ሳሪስ ፣ አስኮ፣ ኮልፌ አጠና ተራ፣ ዘነበ ወርቅ፣ ታይዋን ሰፈርና በመሳሰሉ የከተማዋ የንግድ አካባቢዎች ነጋዴዎች ድርጅቶቻቸውን ሲዘጉ፣ በዋናው የገበያ ማእከል ግን ድርጅቶቻቸውን መዝጋት በሚፈልጉ እና በማይፈልጉ ነጋዴዎች መካከል የእርስ በርስ መጠራጠር በመስፈኑ የአድማውን ጥሪ እስካሁን ተግባራዊ አለማድረጋቸውን አንዳንድ ነጋዴዎች ገልጸዋል። በተለያዩ አካባቢዎች ህወሃት ያሰማራቸው በነጋዴ ስም የሚንቀሳቀሱ የፓርቲው የመረጃ ሰዎች፣ የነጋዴዎችን እንቅስቃሴ በቅርበት እየተከታተሉ ቢሆንም፣ አንዳንድ ነጋዴዎች ከሰአት በሁዋላ አድማውን ተቀላቅለዋል። ዘጋቢያችን በመርካቶም የተዘጉ ሱቆችን ማየቱን ገልጿል።
ተባባሪ ሪፖርተራችን በመርካቶ ውስጥ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው መደብራቸውን ከፍተው ያገኛቸው ሌሎች የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ‹‹ በውስጣችን በተሰገሰጉ ጆሮ ጠቢዎች እንደልብ መረጃ መለዋወጥ አዳጋች በመሆኑ እንጂ እኛም በቀጣይ እንደምንቀላቀላቸው ግልጽ ነው፡፡ የመንግስት ባለስልጣናት ሳያማክሩን በኃይልና ሥልጣናቸው ተመክተው የጣሉብን የገቢ ግምት የማይቃወሙ ቢኖሩ ከባለጊዜዎች ጋር የተለየ ሰንሰለት ዘርግተው የሚሰሩ ብቻ ናቸው ፤ እነርሱ ደግሞ በመከላከያ መኪና ኮንትሮባንድ እየመጣ በግልጽ የሚራገፍላቸው እንደመሆኑ ከገቢያቸው አንጻር ምንም ቢጠየቁ አይከብዳቸውም፣ ወይም ባላቸው ሰንሰለት ምንም ላይጠየቁ ይችላሉ ›› ይላሉ።
በመርካቶ ውስጥ ያለውን አድሎኣዊ የንግድ አሰራር ሲያስረዱም ‹‹ ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች በቀጥታ ከሶማሌ አርቲሼክ ፣ወይም በኬንያ ድንበር ከሞያሌ በመከላከያ መኪኖች ተጭኖ በእኩለ ቀን እያየን ከህወሃት ደጋፊ ነጋዴዎች መጋዘንና ሱቅ ይራገፋል፤ ከነዚህ ገዝተን በሱቆቻችን ያኖርነው ኮንትሮባንድ ተብሎ ይነጠቃል፤ የእነርሱ ሲራገፍም ሆነ ለእኛ ሲሸጥ ጠያቂ የለውም፡፡ የተዘረፍነው በየት በኩል እንደሆነ በማናውቀው ሁኔታ ተመልሶ እጃቸው ገብቶ ዳግም ይሸጥልናል፡፡ በዚህ መልክ ከንግዱ ሊያወጡን በተቃረቡበት ሁኔታ አሁን ደግሞ በግብር መልክ መጡብን›› በማለት ምሬታቸውን ይናገራሉ፡፡
‹‹ በአንድነት ይህን ሁኔታ ከመቃወም ሌላ በግል ቅሬታ አቅርቡ የሚለው አይሰራም… አውቀው በዕቅድ የሚያደርጉትን በግል በተናጠል ሄደን የምናገኘው መፍትሄ የለም፡፡ በቀጣይ ተቃውሞውን በጋራ የጀመሩትን ወንድሞቻችን ከመቀላቀል ሌላ አማራጭ የለንም›› ሲሉ በሌሎች የመርካቶ አካባቢ ያሉ ነጋዴዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በታይዋን አካባቢ ያላቸውን መደብር የዘጉት ነጋዴዎች በበኩላቸው ‹‹ ለተቃውሞአቸው አሳማኝ ምላሽ እስከሚያገኙ ›› በአድማው እንደሚገፉበት ይገልጻሉ።
ወደ ሌሎች ከተሞች ስንሸጋገር ደግሞ እንደ ሰሞኑ ሁሉ በአምቦ ዛሬም የተጠናከረ ተቃውሞ ተካሂዷል። ከተማዋ በወታደሮች በመወረሩዋ ወታደራዊ ካምፕ መምሰሏን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
የንግድ ድርጅቶችን በመዝጋት የሚደረገው አድማ እስካሁን ወደ ሃይል የተሸጋገረው በጊንጪ ሲሆን፣ የገዢውን ፓርቲ ማስፈራሪያ በመቀበል ስራ ለመጀመር ሙከራ ያደረጉ አንዳንድ አሽከርካሪዎች፣ አድማውን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ካለው አብዛኛው ነጋዴ ጋር ተጋጭተዋል። በዚሁ ከተማ መኪኖች መቃጠላቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በባሌ፣ ሻሸመኔ፣ መንዲና ነጆም እንዲሁ አድማው በጠነከረ ሁኔታ በመካሄድ ላይ ነው። አድማው ወደ አደባባይ ተቃውሞ ሊለወጥ ይችላል በሚል ስጋት የአጋዚ ልዩ ሃይል አባላት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች መንቀሳቀስ ጀምረዋል። ወታደሮቹ ምንም እንኳ እስካሁን በግለሰቦች ላይ የወሰዱት የሃይል እርምጃ ባይኖርም፣ የአካባቢው ሹሞች የተለያዩ የንግድ ድርጅቶችን እየዞሩ ሲያሽጉ ጥቃት እንዳይደርስባቸው ጥበቃ ሲያካሂዱ ታይተዋል።