ጥር ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መስተዳድሩ መኪኖችን የገዛው በተለያዩ የሃላፊነት ደረጃ ላይ ለሚገኙት ሰራተኞቹ ነው። ከተገዙት መኪኖች መካከል 18፣ የ2013 ምርት የሆ ኑ ፕራዶ መኪኖች፣ 2 መቶ 40 ባለ ሁለት ጋቢና ማዝዳ ፒክ አፕ፣ 27 ያሪስ ቶዮታ መኪኖች የቢሮ ሃላፊዎች፣ም/ቢሮ ሃላፊዎችና ፣የክፍለ ከተማና ወረዳ አመራሮች እንዲሁም የካቢኔ አባላት እንዲጠቀሙባቸው አየተሰራጩ ነው።
መኪኖቹ በጉምሩክ በኩል ከገቡ በኋላ ለስርጭት እንዲያመች በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ግቢ የተደረደሩ ሲሆን ከዚህ በፊት መኪና ለነበራቸውና ለተወሰኑ የተሻሉ የካቢኔ አባላት ለሆኑት በተለይ ለከንቲባው አማካሪዎችና ለፋይናንስና ኢኮኖሚ ቢሮ ኃላፊ ቀድም ብሎ ይዘውት የነበረውን መኪኖች በኢዲሶቹ PRADO መኪኖች የተቀየረላቸው ሲሆን፣ መኪኖቹ የደረሳቸው የተለያዩ በአስተዳደሩ የሚገኙ የቢሮ ኃላፊዎችና የክ/ከተማ አመራሮች ለተረከቡት መኪኖች ኮድ 2 እና 3 ታርጋ እንዲወጣላቸው በመጠየቃቸው ከመንገድ ትራንስፖርት ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል።
ለመንግስት መኪኖች የሚሰጠው ታርጋ ኮድ 4 አዲስ አበባ ቢሆንም ባለስልጣኖቹ ኮድ 2 እና 3 ታርጋ እንዲወጣላቸው የጠየቁበት ምክንያት ለቅንጦትና ለድህንነታቸው ሲባል መሆኑን የመስተዳድሩ ሰራተኞች ይናገራሉ።
ምርጫው ሲቃረብ በተለይ የፓለቲካ ንቅናቄ ስራ ላይ ለሚሳተፉት አመራሮች ለሚያሽከረክሩት መኪና እንደፍላጎታቸው እንዲንቀሳቀሱ ከአንድ በላይ የሠሌዳ ቁጥር ሊፈቀድላቸው እንደሚቸል ምንጮች ይናገራሉ።
መኪኖቹ በምን ያክል ዋጋ እንደተገዙ ለማወቅ የተደረገው ጥረት አልተሳካም። ይሁን እንጅ የተለያዩ ኩባንያዎችን የመሸጫ ዋጋ በመቃኝ ለመረዳት እንደተቻለው የ2010 ሞዴል ፕራዶ መኪና የመሸጫ ዋጋ ከ 55 ሺ እስከ 90 ሺ ዶላር ወይም ከአንድ ሚሊዮን ብር እስ ከአንድ ሚሊዮን 800 ሺ ብር ያወጣል። መስተዳድሩ ለአጠቃላይ የመኪኖቹ ግዢ የወቅቱን የመኪኖች መሸጫ ዋጋ ተንተርሶ ከ70 እስከ 100 ሚሊዮን ብር ሊያወጣ እንደሚችል የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ገልጿል።