የአዲስ አበባ ህዝብ ብሄር የማይጠቀስበት መታወቂያ ሊያገኝ ነው
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 24 ቀን 2010 ዓ/ም ) መስተዳድሩ የመታወቂያ አሰጣጥ መመሪያ ቁጥር 3/2010ን በማሻሻል፣ ለነዋሪዎች ብሄርን የማይጠቅስ መታወቂያ ለማደል በመዘጋጀት ላይ ነው። ከ27 አመታት በሁዋላ ብሄር ያልተጠቀሰበት መታወቂያ በመያዝ የአዲስ አበባ ህዝብ የመጀመሪያ ይሆናል።
መታወቂያ ላይ ብሄርን መጥቀስ ልዩነትን የሚያሰፋ፣ ግለሰቦች በብሄራቸው እየተለዩ ጥቃት እንዲደርስባቸው የሚያደርግና ኢትዮጵያዊነትን አሳንሶ ብሄርን የሚያጎላ ፣በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ አንድነትና ለዜጎች ህብረት የማይጠቅም ነው በሚል ትችት ሲቀርብ ቆይቷል።
አዲስ የተሾሙት የአዲስ አበባ መክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ብሄርን ከመታወቂያ ላይ ማንሳታቸው በነዋሪዎች ዘንድ ድጋፍ እያስገኘላቸው ነው።
ዶ/ር አብይ ጠ/ሚኒስትር ሲሆኑ የኢትዮጵያን አንድነትና የህዝቦችን ትስስር ለማጠናከር የገቡትን ቃል በተለያዩ ፖሊሲዎች ተግባራዊ እያደረጉ መሆኑን ፖሊሲዎቸውን የሚደግፉ ዜጎች ይናገራሉ።
የአዲስ አበባ መስተዳደር የወሰደው እርምጃ በሌሎችም የክልል እና የፌደራል ከተሞች ተግባራዊ እንዲሆን ግፊቶች ቀጥለዋል። እስካሁን ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ይህን አሰራር ለመለወጥ ያቀደ ክልል ስለመኖሩ የታወቀ ነገር የለም።