የአዲስ አበባ ህዝብ ለቀረበት ጥያቄ መልስ እንዲሰጥ አንድነት ፓርቲ ጠየቀ

መጋቢት ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የፓርቲው የአዲስ አበባ ስራ አስፈጻሚ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ‹‹በህገ ወጥ መንገድ የሚቀለበስ ሰላማዊ የትግል ስልት ባለመኖሩ የአዲስ አበባ ህዝብ ለቀረበለት የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ምላሹን እንዲሰጥ ጠይቋል።

የሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ክፍል ህገ ወጥ ደብዳቤ በመጻፍ ሰልፉን ማከናወን አትችሉም ማለቱ ከህግ በላይ መሆኑን እንደሚያሳይ ፓርቲው ገልጿል። መጋቢት 28 ቀን 2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንዲደረግ ቀጠሮ የተያዘለት ሰላማዊ ሰልፍ በተያዘለት ቀጠሮ እንደሚከናወንም ፓርቲው ግልጽ አድርጓል።

የእሪታ ቀን በሚል መሪቃል የሚካሄደው ተቃውሞ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን በተለይም የውሃ፣ መብራት፣ ስልክና የትራንስፖርት ችግሮች እንዲቀረፉ ያለመ ነው።

ህገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን እንዲያገለግል ኃላፊነት የተሰጠው አካል ህጋዊ እውቅና ካገኘ ተፎካካሪ ፓርቲ የሚቀርብለትን ደብዳቤ አልቀበልም ማለቱ ህገ ወጥ ተግባር በመሆኑ ግለሰቡ በመደበኛ ፍርድ ቤት ክስ እንዲመሰረትባቸው ፓርቲው ወስኗል።

ለህግና ህገ መንግሥታዊነት ጥብቅና ለመቆም ቃል የገቡት የፌዴራልና የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊሶች ህግን አክብሮ እየተንቀሳቀሰ ከሚገኘው ፓርቲው ጎን እንዲቆሙ ጥሪ ያቀረበው አንድነት፣  በሠላማዊ ሠልፍ ለሚደርስ ማናቸውም አይነት ኪሳራዎች፣ ጉዳቶችና መጉላላቶች ተጠያቂው ህጋዊ ቢሮ ይዞ ህገ ወጥ አሰራር የሚከተለው አካል መሆኑን ግልጽ አድርጓል።

ፓርቲው በአቋም መግለጫው መጨረሻ የውሃ፣ የመብራት፣ የስልክ ችግር የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ከሆነ ውሎ ማደሩን በመግለጽ፣  የቅስቀሳ ስራውም ከዛሬ መጋቢት 24 ቀን 2ዐዐ6 ዓም ጀምሮ በይፋ እንደሚጀመር ግልጽ አድርጓል።