በአዋሳ ታቦር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተነሳ ግጭት ተማሪዎች ተጎዱ

መጋቢት ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከቋንቋ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በተነሳው ግጭት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ተማሪዎች ከቀላል እስከ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የፌደራል ፖሊስ አባላት ከትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ የሚወጡ ተማሪዎችን ሲደበድቡ የታዩ ሲሆን፣ በውስጥ ያሉ ተማሪዎችም እንዲሁ ድንጋይ ሲወረወሩ መታየታቸውን የአይን እማኞች ገልጸዋል።

ግጭቱ ተባብሶ በመሄዱ የፌደራል ፖሊስ አባላት ጥይቶችን በተደጋጋሚ ተኩሰዋል። ታቦር ትምህርት ቤት መዘጋቱንም ለማወቅ ተችሎአል።

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሰው ከግጭቶች ጀርባ የአካባቢው ባለስልጣናት እጅ አለበት ይላሉ።በተለይም አዋሳን ወደ ፌደራሉ መንግስት ለማዘዋወር በማሰብ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የስም ለውጦች ማድረግ በመጀመሩ ግጭቱ እንደተነሳ የሚናገሩት ወገኖች፣ ተማሪዎች ያኑሰዋቸው ጥያቄዎች በቀላሉ የሚፈቱ ሆነው ሳለ የመንግስት ባለስልጣናት ዝምታን መምረጣቸው ከግጭቱ ጀርባ እጃቸው እንዳለበት ያመላክታል ይላሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ከማንነት ጋር በተያያዘ እየታየ ያለው ችግር ካለፉት 5 አመታት ጀምሮ እየተጠናከረ መምጣቱን የሚናገሩት አንዳንድ ነዋሪዎች፣ በተማሪዎች የተነሳው ግጭት ከቋንቋ ጋር ብቻ መታየት እንደሌለበትና ችግሩ ስር እየሰደደ የመጣ ጉዳይ መሆኑን በማስታወስ ያስጠነቀቅቃሉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ እየታየ ለመጣው ከማንነትና ከጎሳ ጋር በተያያዘ ለሚፈጠሩ ችግሮች አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ከመጪው ምርጫ ጋር ሲያያይዙት ሌሎች ወገኖች ደግሞ ገዢው ፓርቲ የሚከተለው የብሄር ፖለቲካ አስከፊ ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑን ያስጠነቅቃሉ።

በባህርዳር በተደረገው የክልሎች የስፖርት ጨዋታ ላይ የስነምግባር ጉድለት መታየቱ፣ በጉጂና በቦረናዎች መካከል  ግጭት መነሳቱ፣ በሻኪሶ በተነሳ ረብሻ ጉዳት መድረሱ ይታወቃል።