ጥቅምት ፫(ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአስተዳደሩ የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽ/ቤት ቅዳሜ ዕለት ይፋ ባደረገው የጨረታ ውጤት መሠረት በቦሌ ክፍለከተማ ለአንድ ካሬሜትር መሬት ቦታ አሸናፊ የሆነው ግለሰብ ለካሬሜትር 55ሺህ 597 ብር ከ65 ሳንቲም የሰጠ ሲሆን
ግለሰቡ አሸናፊ የሆኑበት 403 ካሬሜትር ገንዘብ ሲሰላ 22 ሚሊየን 405ሺህ 852 ከ95 ሳንቲም ሆኗል፡፡
በዚሁ ክፍለከተማ ለጨረታ ከቀረቡት 38 ቦታዎች መካከል በዝቅተኛ ዋጋ ያሸነፈው ግለሰብ የሰጠው ገንዘብ በካሬሜትር 3ሺህ 228 ብር ሲሆን ከከፍተኛ ዋጋው ጋር ሲነጻጸር በአንድ ካሬሜትር የ52 ሺህ 369 ብር ከ65 ሳንቲም ከፍተኛ ልዩነት ማሳየቱ በአዲስአበባ ከተማ ትልቅ
የመነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል፡፡
አስተዳደሩ የአሸናፊዎችን ዝርዝር ይፋ ባደረገበት መረጃ ላይ በሌሎች ክፍለከተሞች ማለትም በንፋስስልክ ላፍቶ ለአንድ ካሬሜትር ብር 12ሺ 500፣ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ ለአንድ ካሬሜትር ብር 5ሺህ 750 ከፍተኛ ዋጋዎች የሰጡ ግለሰቦች አሸናፊ ሆነዋል፡፡
አንድ የአዲስአበባ ከተማ ነዋሪ ከዚሁ የጨረታ ውጤት ጋር በተያያዘ በሰጡት አስተያየት የአዲስአበባ የመሬት ሊዝ ዋጋ ከጊዜ ወደጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየተወደደ መምጣቱን አስታውሰው አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች በሊዝ ቦታ ወስደው እንደአቅማቸው የመኖሪያ ቤት መገንባት
ፍላጎታቸው ጨርሶ የማይቻል እየሆነ መምጣቱን አሳሳቢ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ መንግስት ገቢ ከመሰብሰብ ባለፈ በዜጎች መካከል ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ትኩረት አለማድረጉ የብዙሃኑን ተጠቃሚነት በመጉዳት ጥቂት ሀብታሞችና በሙስና ገንዘብ ያከማቹ ግለሰቦችን ወደመጥቀም
ያጋደለ አሰራር እንዲሰፍን ምክንያት መሆኑን ይህ ኢፍትሀዊ አሰራር ቆይቶም ቢሆን ዋጋ የሚከፍልበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በአዲስአበባ ከተማ በ22 ሚሊየን ብር ቦታ ከነሕንጻው መግዛት እንደሚቻል የጠቆሙት እኚሁ አስተያየት ሰጪ ለባዶ ቦታ ከ22 ሚሊየን ብር በላይ የሚከፍሉ ተጫራቶች የፋይናንስ ምንጫቸው በደንብ ሊጠና ይገባል ብለዋል፡፡