የካቲት ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ የከተማዋ ሕዝብ ብዛት 2 ነጥብ 5 ሚሊየን መሆኑን ከሁለት ዓመት በፊት ይፋ
ማድረጉን ተከትሎ በበርካታ ሕዝብ ዘንድ የአሃዙ ማነስ በጥርጣሬ ከመታየቱ በተጨማሪ በኤጀንሲው ላይ ተከታታይ
ትችቶች ከቆየ በኋላ ዛሬ የህዝብ ብዛቱ አምስት ሚሊየን ደርሶአል ተብሏል፡፡
በዛሬው ዕለት የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ በተገኙበት በአዲስአበባ ደሳለኝ ሆቴል
በተካሄደውና ነገም ቀጥሎ በሚውለው በአዲስአበባና በዙሪያዋ በሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች የጋራ ልማት መሪ ፕላን
የምክክር መድረክ ላይ በቀረበው ጥናት የከተማዋ ሕዝብ ብዛት ዘንድሮ አምስት ሚሊየን መድረሱን፣በቀጣይ 10
ዓመታት ሰባት ሚሊየን ፣በቀጣይ 25 ዓመታት ወደ 13 ሚሊየን እንደሚያድግ ተገልጾአል፡፡
ይህን መነሻ በማድረግም የከተማዋ ልማት በዙሪያዋ ያሉትን የኦሮሚያ አጎራባች ከተሞች ማለትም ለገጣፎ፣ለገዳዲ፣ሰበታ፣ቡራዩ፣ገላን ከተሞች ጋር በተቀናጀ መልኩ ለማካሄድ የሚረዳና እስከ 20 ዓመታት የሚቆይ መሪ ፕላን ዝግጅት መጀመሩን ተነግሯል፡፡
በተለይ የአዲስአበባ ሕዝብ ቁጥር ማዕከላዊ ስታስቲክስ ካወጣው በተቃረነ መልኩ እንዴት ሊገለጽ እንደቻለ
በስብሰባው ላይ ተጠይቆ የከተማው ህዝብ ብዛት አምስት ሚሊየን መሆኑ ከኤጀንሲው የተገኘ መረጃ መሆኑን የቀጣዩ
ኣመታት ትንበያ ግን በባለሙያዎች ግምት የተሰራ መሆኑ ተነግሯል፡፡
የአዲስአበባ እና የኦሮሚያ አጎራባች ከተሞች አለመቀናጀት ሐብትን በጋራና በቁጠባ ለመጠቀም ካለማስቻሉም ባሻገር
ልማትን በመደጋገፍና በጋራ ለማካሄድ አላስቻለም፡፡በአሁኑ ከፍተኛ የመሰረተ ልማት እጥረትና ድህነት ለአዲስአበባ
ቅርብ በሆኑ የኦሮሚያ ከተሞች እንደሚታይ በጥናት መረጋገጡን በስብሰባው ላይ የተመለከተ ሲሆን ትብብሩ ይህን
ችግር ለመቅረፍ ያግዛል ተብሎአል፡፡
በስብሰባው ላይ መሪ ፕላኑ ተዘጋጅቶ በሚተገበርበት ወቅት እንደመልካም አስተዳደር፣ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት
ዓይነት ችግሮች የማይፈቱ ከሆነ ትልቅ እንቅፋት እንደሚሆን፤በመሆኑም ፕላኑ ከወዲሁ ለችግሩ እልባት ማስቀመጥ
እንደሚገባው ተሰብሳቢዎች አስተያየት ቀርቦአል፡፡
ከኦሮሚያ ክልል እንደመጡ የገለጹ አንድ አስተያየት ሰጪ የጋራ መሪ ፕላን በአዲስአበባ እና በኦሮሚያ ክልሎች
ሲዘጋጅ ሕዝቡ ተጠይቋል ወይ፣እንዴት መቶ ሰዎች ተሰብስበው በ40 ሚሊየን ኦሮሚያ ህዝብ ዕጣ ፈንታ ላይ ይወስናሉ
ሲሉ ተቃውሞአቸውን አስምተዋል፡፡አያይዘውም ኦሮሚያ ከአዲስአበባ ማግኘት ያለባት ጥቅም እያገኘት ባልሆነችበት
ሁኔታ በጋራ ልማት ስም የኦሮሚያ መሬት ሊዘረፍ ነው ወይ ማለታቸው በተሰብሳቢው ዘንድ ጉምጉምታን አስከትሏል፡፡
በ1997 ምርጫ ቅንጅት አዲስ አበባን ባሸነፈበት ወቅት ኢህአዴግ የነዋሪውን ህዝብ ቁጥር ዝቅ ለማድረግ ተገዶ ነበር። ተቃዋሚዎች በአዲስ አበባ እንደማይወዳደሩ ማስታወቃቸው ምናልባትም ኢህአዴግ የህዝብ ቁጥሩን ለመጨመር ሳይፈልግ እንዳልቀረ የዘጋቢያችን ሪፖርት ያመለክታል።