የአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ እናቶችን እና ለጋ አራሶችን ጤና ለማሻሻል 40 ሚልዮን ዩሮ ለገሰ

ሚያዚያ ፲ (አስር) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአውሮፓ ኅብረት “በኢትዮጵያ በሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎች የማዋለድ አገልግሎት ማሻሻያ ፕሮጀክት በሚሰኘው ፕሮጀክት በኩል ለፌደራል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የ40 ሚልዮን ዩሮ ልገሳ ማበርከቱን አስታውቋል፡፡

ከአውሮፓ ኅብረት የተበረከተው አዲሱ ልገሳ በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የእናቶችን ጤና እና የለጋ አራሶችን ክብካቤ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ይውላል፡፡ ከዚህ ልገሳ ውስጥ፤ 20 ሚልዮን ዩሮ ያህሉ ለፌደራል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚሊንዬም የልማት ግቦች  የገንዘብ ቋት የሚመደብ ሲሆን፤ የተቀረው ገሚሱ ደግሞ ለዩኒሴፍ የሚበረከት ነው፡፡

በአውሮፓ ኅብረት፣ በፌደራል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ እና በዩኒሴፍ መካከል የተዘረጋው ይህ አዲስ የእናቶች ጤና ውጥን፤ እስካሁን የእናቶች ጤናን ለማሻሻል ለኢትዮጵያ ከተበረከቱት ግዙፍ ልገሳዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ለእናቶች እና ለለጋ አራሶች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ደረጃ ለማላቅ የተወጠነው በኢትዮጵያ በሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎች የማዋለድ አገልግሎት ማሻሻያ ፕሮጀክት” በፌደራል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና በዩኒሴፍ አማካኝነት፤ እንዲሁም በእናቶች እና በለጋ አራሶች ዙሪያ በሚሠሩ ሌሎች የልማት አጋሮች እና የጤና ባለሙያዎች ማኅበራት ድጋፍ በጋራ የሚተገበር ይሆናል፡፡

“በበርካታ የጤና አመላካቾች ረገድ ኢትዮጵያ ከፍተኛ እመርታ ብትጨብጥም፤ የእናቶች ሞት መጣኔን ማሻሻል ግን ዓይነተኛ ተግዳሮት ሆኗል” በማለት የአውሮፓ ኅብረት ልኡክ በኢትዮጵያ ኃላፊ አምባሳደር ቻንታል ሄበርችት ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ማሻሻያውን ለማፋጠን ከፌደራል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና ከዩኒሴፍ ጋር በአብሮነት ለመሥራት የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ 40 ሚልዮን ዩሮ ልገሳ ማበርከቱን ተናግረዋል።