የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ሁኔታ አሳስቦኛል አለ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 12/2010)

የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ሁኔታ ስጋት ውስጥ እንደከተተው አስታወቀ።

ትላንት በህብረቱ ቃል አቀባይ የተላለፈው መልዕክት ላይ እንደተገለጸው የአውሮፓ ሀገራት ህብረት በኢትዮጵያ ያለው ብሄርን መሰረት ያደረገው አለመረጋጋት አሳሳቢ ሆኖበታል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎችና በዩኒቨርስቲዎች የሚታየው የሰላም መደፍረስ ስጋት ውስጥ እንደከተተው ህብረቱ ትላንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በተለይም በሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች መሀል የተፈጠረው ግጭት የማያባራ ሆኖ መቀጠል በከፍተኛ ሁኔታ አሳስቦኛል ብሏል የአውሮፓ ህብረት።

የህብረቱ የውጭ ጉዳዮችና የደህንነት ፖሊሲ ቃል አቀባይ ካትሪን ሬይ እንዳስታወቁት በብሄር የተነሳ በኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለው መጠነ ሰፊ ግጭት የሰው ህይወት ጥፋትና ከፍተኛ የንብረት ውድመት ማስከተሉ የአውሮፓ ህብረትን በእጅጉ አሳስቦታል።

በግጭቶቹ የተነሳ ህይወታቸውን ላጡ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች የሀዘን መልዕክት ያደረሱት ቃል አቀባይዋ ገለልተኛና ነጻ አጣሪ ኮሚሽን በአስቸኳይ ተቋቁሙ ጉዳዩን በማጣራት አስፈላጊው ርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አድርገዋል።

ቃል አቀባይዋ ሁሉም ወገኖች የፌደራል ፖሊስና የየክልሎቹ ታጣቂ ሃይሎችን ጨምሮ ራሳቸውን እንዲያቅቡም ጠይቀዋል።

የአውሮፓ ህብረት አሁንም ሁሉንም ያሳተፈ ውይይት እንዲካሄድ የሚያበረታታ መሆኑን በመጥቀስ መንግስት አጠቃላይ የውይይት መድረክ እንዲያመቻች በህብረቱ ስም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በኢትዮጵያ የተከሰተውን ቀውስ በተመለከተ የአሜሪካን መንግስትም ስጋቱን የገለጸ መሆኑ የሚታወስ ነው።

የቀድሞ የአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማት ኽርማን ኮህን የህወሀት መንግስት አሜሪካንን ከተቃዋሚዎች ጋር እንድትሸመግለው ማድረግ አለበት አለበለዚያ ስርዓትና ህግ መፋለሱ አይቀርም ማለታቸው የሚታወስ ነው።

ገለልተኛና ነጻ አጣሪ ኮሚሽን እንዲቋቋም ሲጠይቅ የአውሮፓ ህብረት የመጀመሪያው አይደለም።

የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም በኦሮሚያና አማራ ክልሎች በመንግስት ታጣቂዎች የተፈጸሙትን ግድያዎችና መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚያጣራ ገለልተኛ አካል እንዲቋቋም ጠይቆ በህወሀት መንግስት ውድቅ መደረጉ ይታወሳል።

ትላንት የአውሮፓ ህብረት ላቀረበው ተመሳሳይ ጥያቄ በህወሀት መንግስት በኩል እስከአሁን የተሰጠ ምላሽ የለም።

ባለፈው ዓርብ የአውሮፓ ፓርላማ የተለያዩ የኢትዮጵያ ሃይሎችን በመጋበዝ ማነጋገሩ የሚታወስ ሲሆን በተቃዋሚዎች በኩልም የሽግግር ሰነድ እንደቀረበ ተገልጿል።