የአውሮፓ ህበረት በእነ አቶ አንዱለአም አራጌ ላይ የተላለፈውን ውሳኔ አወገዘ

ሐምሌ ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ህብረቱ ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞችን እና የተቃዋሚ መሪዎችን አወዛጋቢ በሆነው የጸረ ሽብርተኝነት ህግ ሰበብ አድርጎ ማሰሩ በአለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ሳይቀር እንዲተች አድርጎታል።

የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሀላፊ የሆኑት ካተሪና አሽተን የፍርድ ሂደቱን አዲስ አበባ በሚገኙ ዲፕሎማቶች አማካኝነት ሲከታተሉት መቆየታቸውን ያወሳው የህብረቱ መግለጫ፣ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ራሱዋን ከሽብረተኝነት የመከላከል መብት ቢኖራትም ፣  የጸረ ሽብረተኝነት ህጉ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሳይቀር እንደ ሽብር መመልከቱ ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል። ካተሪና አሽተን በእስረኞች ላይ የተላለፈው ውሳኔ በእጅጉ እንዳሳሰባቸው መግለጫው አትቷል።

ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆኑ የአውሮፓ ህብረት ዲፕሎማቶች በኮተኑ ስምምነት መሰረት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በሚያደርጉት ድርድር፣ ለሰብአዊ መብትና ለፕሬስ ነጻነት ትኩረት እንዲሰጡ አሽተን አሳስበዋል።

በአቶ አንዱአለም አራጌ መዝገብ በተከሰሱት ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ላይ የተላለፈውን ውሳኔ የአሜሪካ መንግስትን ጨምሮ በርካታ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች አውግዘውታል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide