ግንቦት ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የአዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሙስሊም ተማሪዎች ትናንት ሐሙስ ግንቦት 2 ቀን ፆማቸውን በመዋል ተቃውሞ በማሰማት ላይ ላሉት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች አጋርነታቸውን አረጋገጡ።
ተማሪዎቹ፤ብዙሀኑ የኢትዮጵያ ሙስሊም ሀይማኖታዊ መብቶቹን ለማስከበር እያደረገ ያለው ትግል የነሱም ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ፤ መብታቸው እስኪከበር ድረስ ከሙስሊም ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጎን እንደሚሰለፉ ገልጠዋል።
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹ ከዚህም ባሻገር መንግስት ያሰማራቸው ታጣቂዎች በአርሲ-አሰሳ መስጅድ ሀይማኖታዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ሲጠይቁ በነበሩ ሰልፈኞች ላይ በመተኮስ ለገደሏቸው ፣ላቆሰሏቸው እና ለደበደቧቸው ሙስሊሞች ያላቸውን ፍቅር እና የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ሙሉ ቀን በመፆም ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው ሙስሊም ተማሪዎች በጁምአ ዋዜማ ሀሙስ ሙሉ ቀን በመፆም ማምሻቸውን በካምፓሳቸው ካፌ ውስጥ አንድ ላይ በመሰባሰብ አፍጥረዋል።
በአዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሙስሊም ተማሪዎች የተጀመረው እና ለብዙሀኑ ሙስሊም አጋርነትን የመግለጽ እንቅስቃሴ፤ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ይዛመታል ተብሎ ይጠበቃል።
እስካሁን የ ዩኒቨርሲው አስተዳደርም ሆነ መንግስት በተማሪዎች ላይ ስለወሰዱት እርምጃ የተሰማ ነገር የለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዛሬው የአንዋር መስጊድ ተቃውሞ ሙስሊሙ በዝምታ ተቃውሞውን እንዲገልጥ በተጠየቀው መሰረት በዝምታ ተቃውሞውን አሰምቷል። የዝምታው ተቃውሞ ለምን እንደተመረጠ ግልጽ ባይሆንም ምናልባት በአዲስ አበባ የሚካሄደውን አለማቀፍ የኢኮኖሚ ጉባኤ ለመካፈል የመጡ እንግዶች እና ጋዜጠኞች ለተቃውሞው ትኩረት በመስጠት እንዳይዘግቡት መንግስት በኮሚቴው ላይ ጫና አሳድሮ ወይም ተማጽኖ ሊሆን ይችላል የሚሉ አስተያየቶች በስፋት ይደመጣሉ።
ሙስሊሙ ለመሪዎቹ ያለው አመኔታ እና የመሪዎቹን መመሪያ ለመፈጸም ዝግጁ መሆኑ ብዙዎችን እያስገረመ መምጣቱን ዘጋቢያችን ገልጧል። መንግስት የሙስሊሙ መሪዎችን ለማሰር ያልደፈረው ህዝቡ ለመሪዎች ያለው ድጋፍ ስላስፈራው ይሆናል የሚሉ አስተያየቶች መኖራቸውንም አክሎ ገልጧል። ___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide