የአክሲዮን ድርሻ የገዙ ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ከባንክና ኢንሹራንስ ዘርፍ እንዲወጡ የጊዜ ቀነ-ገደብ ተሰጣቸው

ኢሳት (ህዳር 6 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ በባንክና በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ የአክሲዮን  ድርሻ የገዙ የውጭ ሃገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ከዘርፉ እንዲወጡ የጊዜ ቀነ-ገደብ ተሰጣቸው።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ትውልደ-ኢትዮጵያውያን የሆኑና የተለያዩ ሃገራት ዜግነት ያገኙ ግለሰቦች በባንክና በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ የአክሲዮን ድርሻን እንዳይገዙና በዘርፉ እንዳይሰማሩ በቅርቡ መመሪያ ማውጣቱ ይታወቃል።

የመመሪያውን ተግባራዊነት በመከታተል ላይ የሚገኘው ባንኩ በቀጣዮቹ 60 ቀናት ውስጥ ሁሉም ትውልደ-ኢትዮጵያውያን የአክሲዮን ድርሻ ሰርቲፊኬታቸውን እንዲመልሱ ማሳሰቡን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2014 መገባደጃ ላይ የብሄራዊ ባንክ ሁሉም የግል ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባያዎች በየድርጅቶቻቸው ውስጥ አክሲዮን ገዝተው ያሉ ግለሰቦችንና ተቋማትን ግንኙነት ለመንግስት አስተላልፈው እንዲሰጡ መመሪያ ማውጣቱ ታውቋል።

በኢትዮጵያ በባንክ ስራ ላይ ተስማርተው የሚገኙ 16 የግል ባንኮችና ሌሎች የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለትውልደ ኢትዮጵያውያኑ የአክሲዮን ድርሻ የገዙበትን ገንዘብ እንዲመልሱ መታዘዛቸውን በሃገር ውስጥ የሚታተሙ ጋዜጦች ዘግበዋል።

ይሁንና ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የባንክ ባለሙያዎች መንግስት ትውልደ-ኢትዮጵያውያኑን ከፋይናንስ ዘርፍ ለማስወጣት የወሰደው ውሳኔ ምክንያቱ ሊገባን አልቻለም ሲሉ ተናግረዋል።

ትውልደ-ኢትዮጵያውያኑ የገዙት የአክሲዮን ድርሻ በብር ብቻ እንዲመለስላቸው የተወሰነ ሲሆን፣ ምን ያህል ግለሰቦች በውጭ ምንዛሪ የአክሲዮን ድርሻን እንደገዙ የታወቀ ነገር የለም።

መንግስት የወሰደው ዕርምጃ በቅርብ በተቋቋሙና አነስተኛ ካፒታል ባላቸው ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችልም የባንክ ባለሙያዎች አስታውቀዋል።

ትውልደ-ኢትዮጵያውያኑ በባንኮቹ ተሰማርተው መቆየታቸው ያስከተለው ጉዳት አልገባንም የሚሉት የባንክ ባለሙያዎች እርምጃው ለዘርፉ ችግሮችን ሊያመጣ እንደሚችልም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ዘመን ባንክ፣ የኦሮሚያ አለም አቀፍ ባንክ፣ አንድነት ኢንሹራንስ ኩባንያን ጨምሮ ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት በድርጅቶቻቸው አክሲዮን የገዙ ትውልደ-ኢትዮጵያውያን በ60 ቀናቶች ውስጥ የአክሲዮን ሰርቲፊኬቶቻቸውን እንዲመልሱ ጥሪ ማቅረባቸው ታውቋል።

በሃገሪቱ ተሰማርተው የሚገኙ ሁሉም የግል ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አፈጻጸማቸውን በተመለከተ ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት እንዲያቀርቡም ታዘዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በዘርፉ እንዲሰማሩ ከፈቀደ በኋላ በምን ምክንያት እርምጃን ሊወስድ እንደቻለ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።