የአንጋፋው ጋዜጠኛ የአቶ ሙሉጌታ ሉሌ የቀብር ስነ-ስርአት በአሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት ተፈጸመ

ኢሳት ዜና (ጥቅምት 27 ፣ 2008)

በዋሺንግተን ዲሲ አቅራቢያ አርሊንግተን በተካሄደው በዚህ የቀብር  ስነ-ስርአትና በአሌክሳንድሪያ ከተማ በተከናወነው የጸሎት ፕሮግራም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ መገኘቱንም ለማየት ተችሏል ።

ከአውሮፓ፣ ከካናዳና፣ ከተለያዩ የአሜሪካ ግዛት የመጡ እንዲሁም በዋሺንግተን ዲሲ ዙሪያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት የጸሎትና የቀበር  ስነ-ስርአት የአቶ ሙሉጌታ ወዳጆች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

የአንጋፋው ጋዜጠኛና ደራሲ እንዲሁም የፖለቲካ ተንታኝ የአቶ ሙሉጌታን ሕልፈት በተመለከተ በተዘጋጀው የጸሎት ስነ-ስርአት ወዳጆቻቸውና ጓደኞቻቸው እንዲሁም የተለያዩ ወገኖች ምስክርነትን ሰጥተዋል። አቶ ሙሉጌታ ሉሌ የህይውት ታሪክም በጋዜጠኛ ደረጀ ደስታ የተነበበ ሲሆን የቪኦኤው ጋዜጠኛ አዲሱ አበበ የዝግጅቱ አስተባባሪ በመሆን ፕሮግራምን የመራ ሲሆን፣ የአቶ ሙሉጌታ ሉሌ የረጅም ዘመን ጓደኛ አቶ ተክለማሪያም መንግስቱ፣ ከለንደን ወደ ዋሺንግተን በመብረር ምስክርነት ሰጥተዋል።

የቀደሞ የማስታወቂያ ሚኒስቴር አቶ መርዕድ በቀለ፣ አርቲስት አለምጸሐይ ወዳጆ፣ እና የ ቪኦኤ ጋዜጠኛ ሰለሞን ክፍሌ ከአቶ ሙሉጌታ ጋር የነበራቸውን ትዝታ እያስታወሱ ምስክርነት ስጥተዋል ። አክቲቪስት ታማኝ በየነ ለስራ ከሚገኝበት ስዊዘርላንድ ሃዘኑን የገለጸ ሲሆን፣ ኢሳት የአቶ ሙሉጌታ ሉሌን ሕልፈት በተመለከተ ያወጣውን መግለጫ በንባብ ተሰጥቷል። በኢሳት የተዘጋጀ አቶ ሙሉጌታን የተመለከተ አጭር ዘጋቢ ፊልምም የቀረበ ሲሆን የአቶ ሙሉጌታ ሉሌ ቤተሰቦችም ድንገት የተለየዋቸውን አቶ ሙሉጌታን አስታውሰዋል።

አንጋፈው ጋዜጠኛና የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ሙሉጌታ ሉሌ ህይወታቸው ያለፈው ባለፈው እሁድ መስከረም 23/2008 እንደነበር ይታወሳል። በዚሁ እያገባደደን ባለነው የመስከረም ወር ብቻ አምስት አንጋፋ ኢትዮጵያውያን ህይውታቸው ማለፉ ይታወሳል። ዶ/ር ሽመልስ ተክለጻዲቅ፣ ኮሎኔል ባጫ ሁንዴ፤ አቶ አቢሴሎም ይህደጎ ፤ አቶ ሙሉጌታ ሉሌ፣ እና አምባሳደር ዘውዴ ረታ በቀናትና በሳምንታት ልዩነት ባለፉት አራት ሳምንታት ህይወታቸው አልፏል። ከኪነጥበብ ባለሙያዎች አርቲስት ሰብለ ተፈራም በአደጋ 1/2008 ሀይወቷ ማለፉ ይታወቃል።