የሃዘን መግለጫ

አቶ ሙሉጌታ ሉሌ

አቶ ሙሉጌታ ሉሌ

መስከረም 27, 2008

አንጋፋው ጋዜጠኛ፣ ሃያሲ፣ ደራሲና፣ የፖለቲካ ተንታኝ ሙሉጌታ ሉሌ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው የኢሳት ማኔጅመንት፣ ጋዜጠኞችና፣ መላው የኢሳት ቤተሰብ ከፍተኛ ሃዘን ተሰምቶታል። አቶ ሙሉጌታ ሉሌ በተባ ብዕራቸው ሃገራዊ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ ነፃነትንና፣ ፍቅርን የሰብኩ፥ በአንደበታቸው ስለኢትዮጵያ የመሰከሩ፣ እስከመጨረሻ እስትንፋሳቸው ድረስ ኢትዮጵያን ያገለገሉና፣ ኢትዮጵያን ተቀምተው በስደት የቀሩ ሃገራዊ ሃብት ነበሩ።

የሙያ አባታችን ሙሉጌታ ሉሌ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ (ኢሳት) ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ፣ ህዝባዊ ተቀባይነትና መልካም ስም፣ ያደረጉት ጉልህ አስተዋፆና የፈጠሩት ተፅዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ፣ በኢሳት ማኔጅመንት፣ ጋዜጠኞችና ደጋፊዎች ዘንድ ሁሌም ደምቀው ሲታሰቡ ይኖራሉ።

አንጋፋው ሙሉጌታ ሉሌ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ሬዲዮ፣ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በመነንና በጦቢያ መፅሔቶች እንዲሁም በኢሳት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ አገልግለዋል። በዚህም ስለሰው ልጅ መብት፣ ስለፍትሃዊነት፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ዲሞክራሲያዊነት ያለመታከት ሲያስተምሩ ኖረዋል። ዛሬ ስለነጻነት  የሚሰብከው አንደበት ቢዘጋም፣ እውነትና እውቀት የሚዘራው ብዕር ቢነጥፍም፣ ስራቸው ህያው ሆኖ ከመቃብር በላይ እሳቸውን ሲያስታውሰን ይኖራል።

ሙሉጌታ ሉሌ እስከመቃብር ደጃፍ የተናገሩላት እና የመሰከሩላትን ሃገራቸው ኢትዮጵያን በነጻነት የማየት ህልማቸው መክኖ፣ አጽማቸው ጭምር በባዕድ አገር መቅረቱ የሚያሳዝንና የሚያስቆጭ ነው። ምንም እንኳን እርሳቸው ያለ ህሊና ወቀሳ በክብር ቢሄዱም፣ የጀመሩት ከፍጻሜ ሳይደርስ የእኛ እዳ ሆኖ ይቀጥላል።

የአንጋፋው ብዕረኛ ሙሉጌታ ሉሌ ርዕይ የሆኑት ነጻነትና ፍትህ በኢትዮጵያ እውን ሲሆኑ፣ በቁጭት የሸኘነውን አጽም በክብር አንስተን ለሃገሩ አፈር ልናበቃው ቃል እንገባለን። በዚህ አጋጣሚ ቤተዘመዶች፣ ወዳጆቹና፣ አድናቂዎቹ ሁሉ ለደረሰባችሁ መሪር ሃዘን መጽናናት ኣየተመኘን በዚህ ቃልኪዳን ከጎናችን እንድትሆኑ ጥሪ እናቀርባለን።

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር

የኢሳት ማኔጅመንት፣ ጋዜጠኞች እና መላው የኢሳት ቤተሰብ