መጋቢት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የአንድነት ፓርቲ የሰሜን ጎንደር የምእራብ አርማጭሆ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አንጋው ተገኘ ቤተሰብ ለመጠየቅ ወደ ጎንደር በመሄድ ላይ እያሉ ታች አርማ ጭሆ ወረዳ ሳንጃ ከተማ ላይ ተይዘው መታሰራቸውን ከስፍራው የደረሰን ዜና አመልክቷል።
ግለሰቡ የተያዙት ከ4 ቀናት በፊት ሲሆን፣ በአሁኑ ሰአት ፍርድ ቤት ሳይቀረቡ በእስር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።
አቶ አንጋው ተገኝ የአስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ ሠራተኛ መሆናቸውን፣ ከአንድ ዓመት በፊት የብአዴን አባል እንዲሆኑ ተጠይቀው እንደ አንድ የመንግስት ሠራተኛ ሙያዊ ሥራ ከመሥራት ውጪ አባል መሆን እንደማልፈልጉ በመናገራቸው አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ተነግሮአቸው እንደነበር ፍኖተ ጋዜጣ በመስከረም 2005 እትሙ ግለሰቡን አነጋገሮ ዘገባ አቅረቦ ነበር።
ጋዜጣው ትናንት በዋጣው እትሙ ደግሞ የምስራቅ ጎጃም የአንድነት ጸሀፊ የሆኑት አቶ ነጋ አበጀ መጋቢት 6 ቀን 2005 ዓ.ም ጠዋት ወደ መስሪያ ቤት ሲሄዱ በመንግስት ሀይሎች ታፍነው ተወስደዋል፡ ፡ አቶ ነጋ አበጀ ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ የታሰሩበትን ቦታ የሚነግራቸው የመንግስት አካል እንዳጡ ባለቤታቸው ወ/ሮ የኔነሽ ክንዴ ተናግረዋል፡፡