ፍርድ ቤት ለእነ ጋዜጠኛ ተመስገን ተጨማሪ ቀነ ቀጠሮ ሰጠ

መጋቢት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 

ኢሳት ዜና:-የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 16ኛ ችሎት ዛሬ ከቀኑ 4 ሰአት ላይ በቀድሞው የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ እና አሁን የ ልእልና ጋዜጣ ዋና ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ክስ ላይ ተሰይሞ መዋሉን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ የቀረቡት 4 ክሶች ቀደም ሲል ፍትህ ጋዜጣ ላይ በጻፋቸው ጽሁፎች እና በአስተናገዳቸው የአምደኞች ጽሁፍ የመንግስትን ስም በማጥፋት ፣ የወጣቶችን አስተሳሰብ ለአመጽ በማነሳሳት፣ በማናወጥ እና በብሄር ብሄረሰቦች ላይ በመቀለድ የሚሉ ናቸው።

በዛሬው ችሎት ላይ የጋዜጠኛ ተመስገን ዋና ጠበቃ አቶ አምሀ መኮንን እንዳስረዱት ” እኛ የምንከላከለው ጉዳይ የአንድ ጋዜጠኛ ተመስገን ክስ ብቻ ሳይሆን ፣ በአገሪቱ ህገመንግስት በግልጽ ተደንግጎ የሚገኘው ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በራሱ ጥቃት ደርሶበታል፣ እየተከበረ አይደለም፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ይህ ህገመንግስታዊ መብት ባለመከበሩ ምክንያት ተጎጂ የሆነ ተከሳሽ ነው፣ ከ 1985 ጀምሮ እንኳን ብንመለከት ስንት ጋዜጦች እና መጽሄቶች ተዘጉ፣ ስንት ጋዜጠኞች ታሰሩ፣ ተሰደዱ የሚለውን ብንመለከት ፣ ካሉት የተዘጉት ጋዜጦችና እና መጽሄቶች ይበልጣሉ፣ በሀገር ውስጥ ከሚገኙት ከሀገር የተሰደዱት እና የታሰሩት ይልቃሉ፣ ይህም የሆነው በህገ መንግስቱ ተደንግጎ የሚገኘው ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በተግባር ባለመተግበሩ እና በመንግስት በመጠቃቱ ነው” በማለት ገልጸዋል።

ጠበቃ አቶ አምሀ ” የእኛ ምስክሮች ከውጭ አገር የሚመጡም ስለሚገኙበት በጊዜ መጣበብ ዛሬ ተሟልተው አልቀረቡልም፣ የድምጽ ማስረጃም ስላለን በአግባቡ ለማስደመጥ እና የሰንድ ማስረጃም ስላለን አንድ ጊዜ ቀጠሮ ቢሰጠን ሁሉንም አሟልተን ማቅረብ ያስችለናል” ሲሉ ፍርድቤቱን ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱም የጠበቃውን ጥያቄ ተቀብሎ ለሚያዚያ 15 ቀን 2005 ዓም ጊዜ ቀጠሮ በመስጠት ችሎቱ ተበትኖአል።

በዛሬው የችሎት ውሎ በርካታ የአገር ውስጥ እና የውጭ ጋዜጠኞች የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ፣ የዲፕሎማሲ ማህበራት አባላት እና የሙያ አጋሮቹ የተገኙ ሲሆን በአዳራሽ ጥበት ምክንያት በርካታ ሰዎች ውጭ ለመቆም ተገደው ነበር።

ጋዜጠኛ ተመስገን ፍትህ ጋዜጣ መዘጋቱን ተከትሎ በአዲስ ታይምስ፣ አሁን ደግሞ በልእልና ጋዜጣ ላይ እየጻፈ ይገኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአቶ በረከት የሚመራው የኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ አዲስ የስም ማጥፋት ዘመቻ መጀመሩን ለጋዜጠኛው ቅርበት ያለቸው ሰዎች ለኢሳት ገልጸዋል።