የአቶ አብዲ አሌ ወኪሎች የለውጥ አራማጆችን ስብሰባ አደናቀፉ
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 4 ቀን 2010 ዓ/ም ) የኢትዮ-ሶማሊ ክልል መሪ የሆኑትን የአቶ አብዲ ሙሃመድ ኡመርን አገዛዝ የሚቃወሙ፣ በክልላቸው ዲሞክራሲያዊ ለውጥ እንዲመጣ የሚታገሉ ከ300 ያላነሱ የአካባቢው ተወላጆች የአገር ሽማግሌዎሎች፣ ከውጭ አገር የመጡ ኢትዮጵያውያንና ምሁራን በሂደት ስለሚወስዷቸው እርምጃዎች የሚመክሩበት ስብሰባ አቶ አብዲ አሌ በላካቸው ሰዎች እንዲጨናገፍ ተደርጓል።
ጠዋት ላይ በአዲስ አበባ ፍሬንድ ሺፕ ኢንተር ናሽናል ሆቴል አዳራሽ በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ ሆቴሉን አስቀድመው የተከራዩ ሰዎች ጩከት በማሰማት ስብሰባው እንዲበጠበጥ ያደረጉ ሲሆን፣ በስፍራው የደረሱ ፖሊሶችም ስብሰባው እንዲቋረጥ አድርገዋል። የመሰብሰብና ሃሳባቸውን በነጻ የመግለጽ መብታቸው መደፈሩን የሚደርስባቸውን ጥቃት በመፍራት ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የስብሰባው አዘጋጆች ተናግረዋል፡፡
የኢትዮ-ሶማሊን ክልል ህዝብ እናድን የሚል አላማ ያነገበው ይህ ስብሰባ ፣ የፌደራል መንግስቱ በክልሉ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ ይጠይቃል። የለውጥ ሃይሎቹ በቀጥታ ወደ ድሬዳዋና ጅግጅጋ ከተሞች በማምራት ህዝቡን አስተባብረው በክልሉ የለውጥ እንቅስቃሴ ለመጀመር እቅድ አላቸው።
የሶማሊን ህዝብ እናድን መድረክ ምስረታ ሰነድ ላይ “የክልሉ ርዕሰ መስተዳደርና ፓርቲው አመራሮች ከስልጣን እንዲወርዱና ስልጣን ለህዝብ ተመልሶ ህዝባዊ መንግስት እንዲቋቋም” የሚጠይቅ ጥሪ ቀርቧል።
ሰሞኑን አለማቀፉ የሰብአዊ መብት ድርጅት ሂውማን ራይትስ ወች በኦጋዴን እስር ቤት ውስጥ የሚፈጸሙ ሰቆቃዎችን ማጋለጡን ተከትሎ የክልሉ ፕሬዚዳንት እስር ቤቱን ዘግተው መስጂድ እንደሚያደርጉት ተናግረዋል። በእስር ቤቱ ለአመታት የቆዩ ሰዎች እየተፈቱ ሌሎችም ወዳልታወቀ ቦታ እየተወሰዱ ነው።