ዛሬ አስቸኳይ ስብሰባ ያደረገው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ መረጠ። አቶ ደመቀ መኮንንን ደግሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የትምህርት ሚኒስትር አድርጎ ሾሟቸዋል።
የፓርላማው አንዱ አጀንዳ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ መሾም መሆኑን ተናግረው ፓርላማውን የከፈቱት አፈ ጉባኤ፣ አቶ አባ ዱላ ገመዳ በተናገሩት መሰረት፤ በአቶ ደመቀ መኮንን ጠቋሚነት፤ አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ ጠቅላይ ሚነስትር ተደርገው ተመርጠዋል።
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ለምርጫ ሲቀርቡ፣ ተቃውሞና ድምፀ-ተዐቅቦ እንዳልተጠየቀ በቴሌቪዥን የተላለፈው ሥርጭት ያሳያል።
በአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ አቅራቢነት አቶ ደመቀ መኮንን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የትምህርት ሚኒስትር ተደርገው ሲታጩ ግን፤ ድምፅ ተዐቅቦና ተቃውሞ ተጠይቆ፤ ሁለቱም ባለመኖሩ፤ አቶ ደመቀ ሹመታቸው በሙሉ ድምጽ ፀድቆላቸዋል።
አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ከሹመታቸው በኃላ ባደረጉት 18 ደቂቃ በፈጀው ንግግራቸው ውስጥ አቶ መለስን “ታላቁ መሪያችን፣ የቁርጥ ቀን የአገራቸው ልጅ” በማለት አሞካሽተዋል።
አቶ መለስ ዜናዊ ከ21 ዓመት በፊት ልትበታተን አንድ ሳምንት የቀራትን ሃገር፤ ከዓለም በፈጣን ሁኔታ ከሚያድጉ ሦስት ኢኮኖሚዎች መካከል አንዷ እንድትሆን አድርገዋል ያሉት አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ፤ የእርሳቸውም ድርሻ የአቶ መለስን ውርስ ሳይበረዝ ማስቀጠል ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ ኃይለማርያም በኢኮኖሚ ዘርፍ፣ በግብርና፣ በውጭ ጉዳይ፤ በኢንዱስትሪና በማኑፋክቹሪንግ ኢህአዴግ ባለፈው 21 ዓመት ሲከተለው የነበረውን ፖሊሲ እንደሚቀጥሉበት ተናግረው፤ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱ መዳበር አስፈላጊ ናቸው ካሏቸው የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመተባበር እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ፤ አንዳንድ በተለያዩ ሽፋን ያአገሪቱን ለላም ሊያደፈርሱ ይጥራሉ የሚሏቸው የሃይማኖትና የፖለቲካ ኃይሎች ላይ ግን አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስዱ ተናግረዋል።
አቶ መለስ ዜናዊ ሥልጣን ላይ በነበሩበት ሰዓት ከተቃዋሚ ኃይሎች ጋር በመተባበር ለመስራት ቃል ቢገቡምና፤ የምርጫ ማስፈጸሚያና ሌሎች ሰነዶችን ከተወሰኑ ተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር ቢፈርሙም፤ በተደጋጋሚ ሕገ-መንግሥታዊውን ሥርዓት ለመናድ ሞክረዋል በሚሏቸው በአገር ቤት የሚገኙ በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ላይ፤ የእስራት እርምጃ መውሰዳቸው ይታወሳል።
አቶ ኀይለማርያም ደሳለኝ፤ በጠቅላይ ፍ/ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ተገኔ ጌታሁን አማካኝነት ቃለ መሀላ ፈጽመዋል።
ከአዲስ አበባ ያነጋገርናቸው ብቸኛ የመድረክ የፓርላማ ተመራጭ፤ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ምክትል ሊቀመንበር፤ አቶ ግርማ ሰይፉ ለኢሳት በሰጡት አጭር ቃለ-ምልልስ፤ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር አብረን ለመስራት አዎንታዊ ምልክት ይሰጣል በሚል ሰበብ የአቶ ኀይለማርያምን መመረጥ፤ እንዳልተቃወሙትና፤ አቶ ሀይለማሪያም መመረጣቸው የለውጥ ተስፋ እንደሰጣቸው ተናግረዋል።