(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 16/2010) የአቶ በረከት ስምኦንና አባዱላ ገመዳ ከስልጣን የመልቀቅ ጥያቄ ያልተለመደ በመሆኑ በሕዝቡ ዘንድ ግርታን ፈጥሯል ሲሉ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም በፓርላማ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ሲመልሱ እንዳሉት አቶ በረከት ከመንግስት ስልጣን ቢለቁም ትግል ትተዋል ማለት ባለመሆኑ ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቷል ብለዋል።
የአቶ አባዱላ ከመንግስት ስልጣን የመልቀቅ ጥያቄ ግን ገና ውይይት እየተደረገበት መሆኑን ነው የገለጹት።
አቶ ሃይለማርያም በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሱሰጡም በመንግስትና በሕዝብ ከሚታወቁ አቋሞች የተለዩ የሚመስሉ አስተያየቶችም ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የአቶ በረከት ስምኦንም ሆነ የአቶ አባዱላ ገመዳ ከመንግስት ስልጣን መልቀቅ ያልተለመደ መሆን በሕዝቡ ዘንድ ግርታን ፈጥሯል ይላሉ።
ይህን ይበሉ እንጂ ሁለቱም ባለስልጣናት ለምን ጥያቄውን እንዳቀረቡ የገለጹት ነገር የለም።
እንደ አቶ ሃይለማርያም ገለጻ አቶ በረከት ስምኦን ከልጅነታቸው ጀምሮ ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ሲታገሉ የነበሩ ናቸው።
ሆኖም ግን ከመንግስት ስራ ለመልቀቅ ተደጋጋሚ ጥያቄ በማቅረባቸውና ይህን ማድረጋቸው ትግል መተው ባለመሆኑ ተፈቅዶላቸዋል ነው ያሉት።
የአቶ አባዱላ ጥያቄ ግን ገና ውይይት እየተደረገበት እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ለፓርላማው ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች የተፈጠረው ግጭት ዋነኛ መንስኤው ጫት ነጋዴዎችና ኮንትሮባንዲስቶች የፈጠሩት ችግር ነው ሲሉም ነው የተናገሩት።
አቶ ሃይለማርያም ይህን ይበሉ እንጂ የፖሊስ አባላትም የአመለካከት ችግር ስላለባቸው የተፈጠረ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
በሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ከፍተኛ ግድያና በመቶሺዎች መፈናቀላቸውን አቶ ሃይለማርያም አልሸሸጉም።
መከላከያ ሰራዊቱ ባይደርስ ኖሮ ከዚህ የበለጠ ጉዳት ይደርስ ነበር ባይ ናቸው።
አቶ ሃይለማርያም ይህ ሁሉ ጉዳት ሲደርስ የመንግስት ምላሽ ለምን ዘገየ ለሚለው ጥያቄ ግን መልስ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ከዚህ ይልቅ ሕዝቡ ለመከላከያ ሰራዊት ወደር የሌለው ፍቅር አለው ሲሉ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ለፓርላማው ገለጻ አድርገዋል።