የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን መንግስት በሚዲያ ስራ እየተመራ ነው አለ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 16/2010)የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መንግስታቸው በሚዲያ ስራ እየተመራ መሆኑን ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሕዝብ መረጃና ዜና የሚሰማው ከአዲስ አበባ ሳይሆን ከዋሽንግተን ዲሲ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርአይ አስገዶም የመንግስት ቃል አቀባዩን ዶክተር ነገሬ ሌንጮን በተቹበት በዚህ መግለጫ የውጭ መገናኛ ብዙሃንን ተጠቅመው ስርአቱን የማብጠልጠልና ግጭቶችን የማባባስ ስራ ከሚዲያዎቹ በስተጀርባ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።

ትልቁ ችግር ከሚዲያው በስተጀርባ የሚሰራ በመሆኑ የማጣራቱ ስራ ተጀምሯል ብለዋል።

በመንግስትና የፓርቲ መገናኛ ተቋማት የተፈጠረው ጤናማ ያልሆነ ፉክክር የቆየ በሽታ ቢሆንም በአሁን ሰአት እየተባባሰ በመሄዱ አደገኛ አዝማሚያዎች እየተፈጠሩ እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

በሀገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ወቅታዊ መረጃዎችን በየጊዜው እየተከታተሉ ባለማድረሳቸው ምክንያት ህዝቡን በውጭ ሀገር ለሚገኙ መገናኛ ብዙሃንና የማህበራዊ ድረ ገጾች እያጋለጧቸው ነው ብለዋል።

አዲስ አበባ አፍንጫ ስር የተፈጸመ ጥፋትን አዲስ አበባ ቁጭ ያለ ሚዲያ የማይሰራው ከሆነና ከዋሽንግተንና ከሌላ የምንሰማ በመሆኑ እየተቀደምን ነው፣እየተመራንም ነው በማለት አቶ ዘርአይ በምሬት ገልጸዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ፋናን በአብነት በማንሳት በህዝቡ ተቃውሞ የጠፋው ሕይወት፣የወደመው ንብረትና የተፈናቀለው ህብረተሰብ ምን ያህል እንደሆነ በግላቸው እንደማያውቁና ዘገባ አለመስራታቸው ትክክል እንዳልሆነ ተናግረዋል።