ህዳር 18 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የአቶ መለስ ዜናዊ መንግሥት በእነ ኤሊያስ ክፍሌ የክስ መዝገብ በ”ሽብርተኝነት ወንጀል‘ የከሰሳቸውን የፖለቲካ ፓርቲ የአመራር አባላትና እና ጋዜጠኞች ተከላከሉ ሲል በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት በኩል ውሳኔ አስተላለፈ፡፡
የፌዴራል ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ለዛሬ ጠዋት ይዞት የነበረውን የችሎት ጊዜ ቀጠሮ ወደ ከሰዓት በኋላ ያስተላለፈ ሲሆን ለዚህም በሰዓቱ ለተገኙት ተከሳሾች፣ የተከሳሽ ቤተሰቦችና የሀገር ውስጥና የውጭ አገር ጋዜጠኞች የሰጠው ምክንያት አልነበረም፡፡
ፍርድ ቤቱ ከሰዓት በኋላ በ9፡30 ሰዓት ላይ በዋለው ችሎት የፌዴራል ዐቃቤ- ሕግ በተከሳሾች ላይ 4 ክሶችን፣ ዘጠኝ የሰው ምሥክሮችን እና የድምጽ እና የምስል ማስረጃዎችን ማቅረቡን አውስቶ የመጀመሪያው ተከሳሽ በአሜሪካን አገር የሚኖረው ጋዜጠኛ ኤሊያስ ክፍሌ በሁሉም ክሶች ሁሉ- በ1ኛ፣ በ2ተኛ፣ በ3ተኛ እና በ4ተኛ ክሶች ተጠያቂ ስለሆነ እንዲከላከል ብይን አስተላልፏል፡፡
ሁለተኛ ተከሳሽ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ (አብዴፓ) ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚሃብሄር በ1ኛ፣ በ2ተኛ እና በ4ተኛ ክሶች፤ ሦስተኛ ተከሳሽ የአውራምባ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ
ውብሸት ታዬ በ1ኛ፣ በ2ተኛ እና በ4ተኛ ክሶች፤ አራተኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ሂሩት ክፍሌ ወልደኢየሱስ በ1ኛ፣ በ3ተኛ እና በ4ተኛ ክሶች፤ አምስተኛ ተከሳሽ የፍትህ ጋዜጣ ዓምደኛ ርዮት ዓለሙ በ1ኛ፣ በ3ተኛ እና በ4ተኛ ክሶች እንዲከላከሉ ወስኗል፡፡
የተከሳሽ ጠበቆችን የመከላከያ ምሥክሮች ለማድመጥ ደግሞ ለታህሳስ 11 ቀን 2004 ዓ.ም ጊዜ ቀጠሮ መያዙን አሳውቋል፡፡
የተከሳሽ ጠበቆች የመከላከያ ምሥክሮቻቸውንና የማስረጃዎቻቸውን ዝርዝር ከታህሳስ 11 ቀን 2004 ዓ.ም ቀደም ብለው ለፍርድ ቤቱ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ በማስተላለፍ በዕለቱ የመከላከያ ምስክሮችን ቃል እንደሚያደምጥ አስታውቋ ችሎቱ ተበትኗል፡፡