አስደንጋጭ ዜና የደረሰው ኢህአዴግ የከተማውን ህዝብ በመከፋፈል ኮንፈረንስ ሊጠራ መሆኑ ታወቀ

ህዳር 16 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-“የአዲስ አበባ ህዝብ በአስተዳደር በደል ምክንያት ከስርአቱ ጋር ሆድና ጀርባ ሆኗል” የሚል አስደንጋጭ ዜና የደረሰው ኢህአዴግ የከተማውን ህዝብ በመከፋፈል ኮንፈረንስ ሊጠራ መሆኑ ታወቀ

የብሄር ብሄረሰቦችን ቀን ምክንያት በማድረግ ገዢው ፓርቲ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በከተማዋና በመላ አገሪቱ ተፈጥረዋል ባለቸው ችግሮች ዙሪያ ውይይት እንደሚያደርግ
የደረሰን ዜና አመልክቷል።

በዚህም መሰረት ህዳር 17 ከንግዱ ማህበረሰብ አባላት ጋር፣ ህዳር 19 ፣ ከፌደራል ሲቪል ሰርቪስ መስሪያ ቤቶች ጋር፣ ህዳር 22 የሴቶች ኮንፈረንስ፣ ህዳር 20 አገር አቀፍ ፍትህ አካላት እንዲሁም ህዳር 24 የወጣቶች ኮንፈረንሶችን ለማካሄድ ማቀዱ ታውቋል።

በእነዚህ ኮንፈረንሶች ላይ የኢህአዴግ አባል ነጋዴዎች፣ ወጣቶች፣ የመንግስት ሰራተኞች ና ዳኞች እንዲሁም፣ የኢህአዴግ አባላት ያልሆኑትም እንደሚገኙ ታውቋል።

ጉባኤው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ለማክበር የሚል ሽፋን ይሰጠ  እንጅ ዋናው አላማው  የአዲስ አበባን ህዝብ ብሶት ማወቅ፣ ከተቻለም አባላትን መመልመል እንዲሁም የኢህአዴግን ህዝባዊ ድጋፍ ማሳዬት ነው ተብሎአል።

ኢህአዴግ ከ5 ሚሊዮን በላይ አባላት እንዳሉት ቢናገርም፣ እጅግ የሚበዛው አባል ለእንጀራው ብሎ ፓርቲውን እንደሚቀላቀል ሂውማን ራይትስ ወችን ጨምሮ በርካታ የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች  ሲዘግቡት ቆይተዋል።

የአዲስ አበባ መስተዳደር ከንቲባ የሆኑት አቶ ኩማ ደመቅሳ የከተማው ህዝብ በአስተዳዳርና በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ነው በማለት መናገራቸው ይታወቃል።